ዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታሰረ

ነሀሴ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዐቃቤ ህግ ፍትህ ጋዜጣ እንዲታገድ ጠይቋል ለብይን ለነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል

ሃሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፡- “ቀደም ሲል ጀምሮ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን የነበረው የለውጥና የነፃነት ጥያቄ የጠቅላይ ሚንሥትሩን ሞት ተከትሎ ተነቃቅቷል፤ ብዙው ሕዝብ ከእንግዲህ ኢህአዴግን ማየት አይፈልግም፤ ይህን የብዙሃን ሕዝብ የለውጥ መንፈስ ጠንቅቆ የሚያውቀው አሁን በግላጭ ወደ ሥልጣን እየመጣ ያለው አምባገነን መንግሥት የሕዝቡን የለውጥ መንፈስ ለማጨናገፍ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል፣ ይህ ሁኔታ አሁንም የሚቀጥል ይመስላል፡፡ የኔም እሥር የዚህ ሁነት ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጥና የነፃነት ቀን በቅርቡ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ የመንግሥት የድንበራ ተግባራት ሥርዓቱ የመጨረሻ የመቃብር ሥፍራው ላይ መድረሱን ያመላክታል፡፡” – የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16 ወንጀል ችሎት የዋስትና መብቱ ተገፎ በፖሊስ ታጅቦ ጊዜያዊ የፍርድ ቤቱ የእሥረኛ ማቆያ የብረት ፍርግርግ ውስጥ ሆኖ በጭብጨባ አድናቆታቸውን ለገለጹለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የተናገረው፡፡

ሃሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም፡- የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና ጋዜጣውን በሚያሳትመው ማስተዋል ህትመትና ማስታወቂያ ኃ/የተ/ የግል ማህበር በተከሰሱበት ሦስት ክሶች /ሕዝቡን የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር/ ወንጀል ዋስትና በመንፈግ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከራከር ፈረደ፡፡

 

በዚሁ ችሎት የኢህአዴግ ልሳን የሆነው የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ አሳታሚና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳምሶም ማሞ እና ባለቤቱ ዘውድነሽ ታደሰ የተከሰሱበት የንግድ ፈቃድ አለማደስ ወንጀል ያለ ዐቃቤ ህግ ስምምነት በፍትህ ሚንስትር ዲኤታ ደብዳቤ ክሱ እንዲቋረጥ መወሰኑን ፍርድ ቤቱ በችሎት ላይ ገልፆል፡፡ ሳምሶን ማሞ ፍርድ ቤቱን አመስግኖ ከባለቤቱ ጋር ከችሎት ወጥቷል፡፡ በአንፃሩ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የዋስትና መብቱ ተገፎ በፖሊስ ታጅቦ የማረሚያ ቤት መኪና እስኪመጣ ድረስ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ጊቢ የብረት ፍርግርግ ውስጥ ተከቷል፡፡

ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ላይ ዘግይቶ የጀመረው ልደታ ምድብ 16 ወንጀል ችሎት በአንድ ዳኛ ብቻ የተሰየመ ሲሆን፣ ዐቃቤያን ሕግ- ብርሃኑ ክንደያ፣ ቴዎድሮስ ባህሩ እና እንዳልካቸው ሙላቱ እና የጋዜጠኛ ተመስገንና የድርጅቱ ጠበቃ ሞላ ዘገየ መኖራቸውን ያረጋገጡት የችሎቱ ዳኛ ባለፈው ነሐሴ 9 ቀን 2004 ዓም ችሎቱ የተላለፈው ዳኛው ለሥራ ጉዳይ በመውጣታቸው ነው በማለት ዛሬም በዝናብ ምክንያት በመዘግየታቸው አዳራሹን ለሞላው የችሎት ታዳሚ ይቅርታ ጠይቀው ክሱን በንባብ አሰምተዋል፡፡

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ ሞላ ዘገየ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ እንደገለጹት ዐቃቤ ህግ ለክሱ ምክንያት ያደረጋቸው ከ1984 እስከ 1987 ዓ.ም ያሉ ሁነቶች በመሆናቸው በይርጋ የተዘጋ ነው፤ ክሱ የቀረበውም በፕረስ ጉዳይ ላይ በመሆኑ ተከሳሹ ሃሳቡን በነፃነት የማንሸራሸር፣ የመተንተን፣ መረጃ የመቀበልና የማሰራጨት አንቀጽ 29 መብቱን ተጠቅሞ አመለካከቱን ስለሆነ የገለጸው ክሱ ውድቅ ይደረግ፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የህገ-መንግስቱ አካል ስለሆኑና ደንበኛዬም ሃሳብን በነጻነት የማራመድ መብቱን በመጠቀሙና ዐቃቤ ህግ የቀረቡት ጽሑፎች የሀሰት ዘገባዎች ናቸው ብሎ ቢከስም ሀሰት ስለመሆናቸው ያስረዳበት ሁኔታ ስለሌለ ይልቁንም ዘገባዎቹ የአደባባይ እውነታ መሆናቸውን በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ተቀባይነት ያላቸው ሃሳቦች በመሆናቸው ክሱ ውድቅ እንዲደረግ እና ክሱ ድግግሞሽ ስለበዛበት እንደገና ተስተካክሎ እንዲቀርብ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

 

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ለክሳችን ምክንያት የሆኑት የ1984 እስከ 1987 ዓ.ም ሁነቶች ሳይሆን የየካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ነሀሴ13 ቀን 2003 ዓ.ም፣ ሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም፣ ታህሳስ 7 ቀን 2004 ዓ.ም እና መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓም የወጡ ጽሑፎችን ይዘት ነው፡፡  በነዚህ ጋዜጦች ላይ የወንጀል ድርጊት ተሰርቷል ነው፣ ይህ ከተፈጸመ ቢበዛ 1 ዓመት እንጂ ከዚያ ስለማያልፍ በይርጋ አይቆምም፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትም ቢሆን ገደብ አለው ፍጹም መብት አይደለም ብሏል፡፡

የችሎቱ ዳኛ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ክርክር ተመልክቷል ካሉ በኋላ ጠበቃው በይርጋ ቆሟል ያሉት ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትም ቢሆን የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ተጠያቂነት እንዳለው በፕረስ ህጉ 590/2000 በግልጽ ተደንግጓል ስለዚህም ይህንንም የጠበቃው መከራከሪያ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም በማለት ሁሉንም መከራከሪያ ውድቅ አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ጥያቄ አቅርቦ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጥፋተኛ አይደለሁም፣ ወንጀለኛም አይደለሁም ያለ ሲሆን ጠበቃ ሞላ ዘገየም የጋዜጣ ድርጅቱን ወክለው ድርጅቱ ጥፋተኛ አይደለም ብለው ቃል ሰጥተዋል፡፡

ዳኛውም ዐቃቤያን ህግ የክስ መክፈቻ ንግግር አድርጉ ብለው በማዘዝ ይህ ክርክር በጋዜጣ ላይ በወጣ ጽሑፍ በመሆኑ በሰው ምስክር ስለማይረጋገጥ በየትኛው ጽሑፍ የቱን ህግ እንደጣሱ አስረዱ ሲሉ አዘዋል፡፡

ሦስቱ ዐቃቤያን ህግ ሞት የማይፈሩ ወጣቶች የሚለው ጽሑፍ በአረቦች ፖለቲካዊ ንቅናቄ ወቅት በኢትዮጵያም እንዲከሰት ወጣቶችን የመቀስቀስ በአረብ ሀገራት ያለው ችግር በእጥፍ በኢትዮጵያም ስላለ በንጉሱ ጊዜ እንዳሉት ወጣቶች ተነሱና ለውጥ አምጡ ብሎ ቀስቅሷል፣ በእርግጥ በጊዜው ወጣቱም አልተነሳምየተባለው ሁኔታም አልተፈጠረም ነገር ግን የመንግስትን ሥም አጥፍተዋል፤ ህወሃት ኢህአዴግ እንዲህ አደረገ እያሉ ስለሚጽፉም አንዱን ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ለማጋጨት ያለመ ነው፣ መጅሊስና ሲኖዶስ ብለው በፃፉትም ኢህአዴግ ጳጳስ ከበረሃ አምጥቶ እንደሾመ- በቅርቡም በጥቂት የሙስሊም ማህበረሰብ ስብስቦች ጥያቄ ላይ መንግስት ለማረጋጋት ሲሰራ ኢህአዴግ በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል እያሉ ጽፈዋል ብለዋል፡፡

ዳኛውም ከዚህ በኋላ የሚቀርብ የሰው ማስረጃ ስለሌለ ግራ ቀኙን መርምረን የጥፋተኝነት ብይን እንሰጣለን ብሏል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃም አንድ ጥያቄ ለዐቃቤ ህግ አለኝ ብለው ዐቃቤ ህግ ለፍትህ ሂደት ይረዳል ይተባበራል እንጂ እንዴት በአንድ ጉዳይ ላይ የሃሳብ፣ የድርጊትና የውጤት ተግባር ሳይታይ ሰው  ላይ ወንጀለኛ ተብሎ ክስ ይቀርብበታል፣ በዚህ ላይ ደንበኛዬ ቃል ያልሰጠበት ሦስተኛ ክስ ቀርቦበታል በማለት ጠይቀው ፍርድ ቤቱ ሁኔታውን መርምሮ ፍትህ ይሰጠናል ብለን እንጠብቃለን በማለት የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ከዚህ ፍርድ ቤት ፍትህን አገኛለሁ ብሎ እንደሚጠብቅ፣ በጊዜ ቀጠሮው አንድም ቀን ዘግይቶና ቀርቶ እንደማያውቅና የአደባባይ ሰው መሆኑን ገልጸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ የዋስትና ጥያቄ ላይ ዳኛው ሲጠይቁ፡- ምንም እንኳ ያቀረብነው ክስ ዋስትና የማይከለክል ቢሆንም ዋስትናውን እንቃወማለን፣ የክስ ቻርጅ ለመስጠት አምስት ቀን ተመላልሰን ነው፣ ያቀረብንባቸው ክስም ተደራራቢ በመሆኑ በቀጠሮ ቀን ይቀርባሉ ብለን ስለማናስብ እና ተከሳሹ ተደራራቢ ድርጊት በሌሎች ጋዜጦችም በፍኖተ ነፃነትና በአዲስ አድማስ ጋዜጦች ላይ መግለጫ እየሰጡ ስለሆነ፣ ከዚህ በፊትም በፍርድ ቤት የታገደ ጋዜጣ አለ ስለዚህ ዋስትናውን እንቃወማለን በማረሚያ ቤት ሆነው ይከራከሩ ብለዋል፡፡

የፌዴራል አቃቤ ህግ በበኩላቸው በመገናኛ ብዙሃን ህግ 590/2000 አንቀጽ42 ንሁስ አንቀጽ 2 መሠረት በብሄራዊ ጉዳይ አደጋ የሚያስከስት ነገር ካለ ዐቃቤ ህግ ህትመቱን ሊያስቆም እንደሚችል ስለሚያትት እስከ ፍርድ ድረስ የፍትህ ጋዜጣ እንዲታገድ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጋዜጣው ተደጋጋሚ ወንጀል ይሰራል በማለት ደምድሟል፡፡ የጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ጠበቃ ሞላ ዘገየም እንዴት ተብሎ ክሳቸውን ሳያሻሽሉ በእግረመንገድ ይጠየቃል ይህ ፍትህን ያዛባል ብለው ተከራክረዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም የመናገር እድል ጠይቆ ክቡር ፍርድ ቤት ዐቃቤ ህግ ሆን ብሎ ፍርድ ቤቱን እያሳሳተ ነው፡፡ ጋዜጣ የሚታገደውም በህጉ መሰረት አደጋ ሊሆን የሚችል ነገር በተጨባጭ ሲያገኝ ነው እንጂ በባዶ ሜዳ ሊሆን ይችላል ተብሎ እንዴት ይሆናል፡፡ ቅድም አምስት ቀን ተመላልሰን ነው መጥሪያ በፖሊስ የሰጠነው የሚሉት ሀሰት ነው፣ ድርጅቱ ህጋዊ ሰውነትና ቢሮ ያለው አድራሻውንም በገሃድ የገለጸ ሆኖ ሳለ ሆን ብለው የቀጠሮው ጊዜ ሁለት ቀን ሲቀረው አጥብበው ነው ጥሪውን የሰጡኝ፣ በአግባቡ የህግ ሰው እንዳላማክር፡፡ በጋዜጣ ላይ መግለጫ ሰጠ ብለው ፍርድ ቤቱን የሚያሳስቱትም ከችሎቱ በፊት ጋዜጦች ሲጠይቁኝ የሰጠሁትን ቃለ መጠይቅ ነው በማለት አስረድቷል፡፡

የችሎቱ ዳኛም የጋዜጣው ይታገድ ጥያቄ ከክሱ በኃላ ይታያል ብለው የዋስትና ጥያቄው ግን ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ተከሳሹ በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከራከር ውሳኔ ሰጥተው የክስ ሂደቱ ለነሐሴ 28 ቀን 2004 ቀጠሮ ተሰጥቶ ችሎቱ ሲበተን ጋዜጠኛ ተመስገን ዳኛውን እና ዐቃቤያን ህጉ በትዝብት እየተመለከተ ነበር፡፡

በፍርድ ቤቱ አድሎ ተፈጽሟል ያሉ የችሎት ታዳሚያን እና የጋዜጠኛውን ክስ ለመከታተል አዳራሽ ሞልቶባቸው በቅጥር ጊቢው ውስጥ የተሰባሰቡ ሰዎች እያለቀሱ (ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ ሴቶችና ሽማግሌዎች) ተመስገን ጀግና፣ አይዞን ከጎንህ ነን፣ የፍትህ ቀን ይመጣል በማለት እስከ ብረት ፍርግርጉ ድረስ በከፍተኛ ጭብጨባ የሸኙት ሲሆን ወላጅ እናቱ እና ቤተሰቦቹ ከኋላ ሆነው ቅዝዝ ብለው ተስተውለዋል፡፡

በሁኔታው የተደናገጡ የጋዜጠኛው ቋሚ ተከታታይ የደህንነት አባላትና 10 የፖሊስ አባላት ወደ መቶ የሚጠጉ የሚያጨበጭቡ ሰዎችን በመቁረጥ ለማስፈራራት ቢሞክሩም ሁኔታው ወደ ሁከት ሊያመራ ሲል በቸልታ አልፈውታል፡፡

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide