ዜግነታቸው ለጊዜው ያልታወቀ ጎብኚ ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 25/2010)

በኢትዮጵያ አፋር ክልል ማንነታቸውና ዜግነታቸው ለጊዜው ያልታወቀ ጎብኚ ተገደሉ።

ጎብኚውን ሲያዘዋውር የነበርው ሹፌርም መገደሉ ታውቋል።

የኢሳት ምንጮች ከስፍራው እንደገለጹት ዛሬ በአፋር ክልል ኤርታሌ በተባለው ወረዳ የተገደሉት ጎብኚ ወደ ኤርታሌ እሳተ ጎመራ በመጓዝ ላይ ነበሩ።

ወደ አካባቢው ሰርገው የገቡት ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ከጎብኚው አጃቢዎችና ከአካባቢው ሃይሎች ጋር መጋጨታቸውም ታውቋል።

ጎብኚው የተገደሉት በተኩስ ልውውጥ ይሁን አልያም ሆን ተብሎ ግን የታወቀ ነገር የለም።

ኢሳት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት እየሞከረ ሲሆን ተጨማሪ መረጃዎችን በቀጣዮቹ ቀናት ለማቅረብ የሚሞክር ይሆናል።

ከአምስት አመት በፊት በዚሁ በአፋር ክልል ኤርታሌ አካባቢ ጎብኝዎችን ለማገት በተደረገ እንቅስቃሴ 5 ጎብኝዎች ሲገደሉ 2 መታገታቸው ይታወሳል።

ዕገታውን የፈጸመው የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዶፍ እንደነበርም ታውቋል።

አርዶፍ በቀናት ውስጥ ባወጣው መግለጫ 2ቱ ጎብኝዎች በእጁ በደህና ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን በመግለጽ 5ቱ ጎብኝዎች የተገደሉት በኢትዮጵያ ወታደሮች ነው ማለቱ ይታወሳል።

ጥር 8/2004 በአፋር ክልል ኤርታሌ ላይ 27 አውሮፓውያን ጎብኝዎች በነበሩበት በተከሰተው ግጭት 2 ጀርመናውያን፣2 ሃንጋሪያውያን፣አንድ ኦስትሪያዊ በድምሩ 5 ጎብኝዎች ተገድለዋል።

የቤልጂየም፣የሃንጋሪና የእንግሊዝ ዜጎች መቁሰላቸው ይታወሳል።

2 ጀርመናውያንና 2 ኢትዮጵያውያን ታግተው የተወሰዱ ሲሆን በኋላም በሃገር ሽማግሌዎች ድርድር መለቀቃቸው አይዘነጋም።

መንግስት በወቅቱ ኤርትራን መወንጀሉ ይታወሳል።