ዚምባቡዌ በሕገወጥ መንገድ ድንበሯን በማቋረጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያቀኑ ነበሩ ያለቻቸውን 38 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን አስታወቀች፡፡

ጥቅምት ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የኬንያው ዴይሊ ኔሽን እንደዘገበው ኢትዮጵያውያኑ የተያዙት ሙታሬ በምትባለውና ከሞዛምቢክ ጋር ድንበርተኛ በሆነችው ከተማ በኩል አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያቀኑ በፖሊስ እንደተያዙ ማክሰኞ ማምሻውን ተዘግቧል፡፡

ተጠርጣሪ ስደተኞቹ በግምት ከ20 እስከ 30 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚምባቡዌ በሕገወጥ መተላለፊያ በኩል መግባታቸውን ያስታወቁት፣ በዚምባቡዌ ቤት ብሪጅ ዲስትሪክት የፖሊስ ኮማንደር ዋና ሱፐር ኢንቴንዳንት ላውረንስ ቺኔንጎ ናቸው፡፡
ፖሊስ ምርመራውን እያካሄደ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑም በሕገወጥ መንገድ ወደ ዚምባቡዌ በመግባታቸው ክስ እንደሚመሠረትባቸው ተናግረዋል፡፡