ዘጠኝ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ትብብር የመጀመሪያ የትግል ስትራቴጂውን ይፋ አደረገ

ጥቅምት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ትብብር የመሰረቱ 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ይፋ አድርገዋል።

‹‹ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለመክፈት የ‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ› በሚል የዝግጅት መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።

‹‹ምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ ያለውን ወገናዊነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ፍንትው አድርጎ ማሳየቱን የገለጹት ፓርቲዎቹ፣  በመጀመሪያ ዙር የአንድ ወር ፕሮግራሙ ከሚፈጽማቸው ጉዳዮች መካከል  በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ ፣

የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን መጥራት፣ በሰላማዊ ሰልፍ የተቃውሞ ድምጾችን ማሰማት፣ በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግ እንዲሁም የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ የሚሉት ይገኙበታል።

በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች 3 የአደባባይ ስብሰባዎች የሚኖሩ ሲሆን፣  ህዳር 27 እና 28 የ24 ሰዓት (የውሎና የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል።

ፓርቲዎቹ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲቀላቀሉዋቸው፣ በአገርውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የአለማቀፍ ማህበረሰቡም ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።