ዕውቁ ፎቶግራፍ አንሽ የሊባኖስ መንግስት ያበረከተላቸውን የክብር ኒሻን መልሶ እንዲረከባቸው ጠየቁ

መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዕውቁ ፎቶግራፍ አንሽ አቶ ሽመልስ ደስታ፤ የሊባኖስ መንግስት 50 ዓመታት በፊት ያበረከተላቸውን የክብር ኒሻን መልሶ እንዲረከባቸው ጠየቁ።

አቶ ሽመልስ ደስታ በዓፄ ሀይለሥላሴ ጊዜ ከሊባኖስ ያገኙትን የክብር ሽልማታቸውን ለመመለስ የወሰኑት፤ ሊባኖስ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ እየተፈፀመ  ያለውን ግፍና በደል በመቃወም ነው።

አቶ ሽመልስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1966 ዓመተ- ምህረት ከቀዳማዊ ሀይለሥላሴ ጋር ወደ ቤሩት ሲያመሩ  ነበር -የወቅቱ የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከራሺድ ካራሚ ለውጪ አገር ዜጎች የሚበረከተውን ታላቁን የክብር ኒሻን ያገኙት።

ይሁንና  በተለይ በሴቶች ኢትዮጵያውያን ላይ ሊባኖስ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው ግፍ እጅግ እያሳዘናቸውና እያንገፈገፋቸው በመጣበት በአሁኑ ጊዜ የክብር ሽልማቱን ይዞ መቀመጥ ለአዕምሯቸው ጤና ሊሰጣቸው እንዳልቻለ የጠቀሱት አቶ ሽመልስ፤ለንደን የሚገኘው የሊባኖስ ኤምባሲ ሽልማቱን እንዲረከባቸው በደብዳቤ  ማመልከታቸውን ደብዳቤውን አባሪ በማድረግ አመልክተዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የ ኢትዮጵያና የሊባኖስ ግንኙነት ጠንካራና መከባበር የነበረበት እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ሽመልስ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አንዳንድ ሀላፊነት የጎደላቸው ሊባኖሳውያን በ ሴት ኢትዮጵያውያን ላይ እየፈፀሙት ያለው ግፍ አሳዛኝና አሣሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

በዚህም ሳቢያ ከሊባኖስ የተበረከተላቸውን የክብር ኒሻንና ዲፕሎማ ለመመለስ ከወሰኑ ወራቶች መቆጠራቸውን የጠቀሱት አቶ ሽመልስ፤ በተለይ በቅርቡ ሊባኖስ ውስጥ በ አሠሪዋ ግፍ ሲደርስባት ለ ዓለም የታየችው ወጣት በተኛችበት ሆስፒታል ሞተች መባሉን ሢሰሙ በውሳኔያቸው መጽናታቸውን ተናግረዋል።

የክብር ሽልማታቸውንና ዲፕሎማቸውን እስከመመለስ ድረስ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የተገደዱትም፤ በ ሴት ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ በ ዓለማቀፉ ህብረተሰብ እንዲታወቅና መፍትሔ እንዲፈለግለት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ስመልስ ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ እየተፈፀመ ስላለው ግፍ የሚዘረዝርና  እና የቤይሩት አስተዳደር ድርጊቱን በአስቸኳይ እንዲያስቆም የሚጠይቅ ማመልከቻ በለንደን የሊባኖስ አምባሳደር ለሆኑት ለሚስተር ኢይናም ኦሰይራን  አስገብተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊቷ ዓለም ደቻሳን ለሞት በመዳረግ ዋነኛ ተጠያቂ ነው ተብሎ በሊባኖስ ፖሊስ ተይዞ የነበረው አሠሪዋ ማህፉዝ ፤ በነፃ እንደተለቀቀ እየተዘገበ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide