ሐምሌ ፲፪ ( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በምግብ እጦት ችግር ምክንያት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ግብረሰናይ ድርጅቶች በጋራ በመተባበር አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ሊያቀርብላቸው ይገባል ሲል የኦሎምፒክ ባለድሉ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተማጽኖውን አሰማ።
ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ተከስቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ ድርቅ ተጠቂ የሆኑና አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች 10.2 ሚሊዮን መሆናቸውንና ይህም አሃዝ ከአስሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ውስጥ አንዱ የርሃብ ተጋላጭ መሆኑን የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) ጥናት አመላክቷል።
”በኢትዮጵያ ጊዜ ሳይሰጠው አፋጣኝ የሆነ የአደጋ ዝግጁነት ስራ መሰራት ይገባዋል። ብዙ ዜጎችቻችን በአሳሳቢ ሁኔታ በርሃብ ስቃይ ውስጥ ናቸው። ዓለም ግን እረስቷቸዋል”
”ድርቁ ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ የሚበሉት ምግብ በማጣታቸው ቤተሰቦች ተበትነዋል። የቤት እንስሳቶችና የጋማ ከብቶቻቸው ሞተዋል፣ ሰብሎቻቸው ወድሞባቸዋል። ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትኩረት ያድርግ። አለበለዚያ ነገሮች ወደ ከፋ መንገድ ይጓዛሉ” ሲል ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ርሃቡን ተከትሎ ሊደርስ ሰለሚችለው ሰብዓዊ ቀውስ አጽኖት ሰጥቶ ተናግሯል።
”ሃገራችን ለውጥ ቢኖርም በድርቁ የተጎዱ ችግረኛ ዜጎቻችን ግን ላለፉት ብዙ ወራቶች ዝናብ አለመጣሉን ተከትሎ ለአስከፊ ርሃብ ተጋልጠዋል። በተለያ ሕጻናትና ነፍሰጡር ሴቶች የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል” ብሏል። የሁለት ጊዜያት የኦሎምፒክ ሜዳይ ተሸላሚ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያንን ሕይወት ለመታደግ ከዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ አክሽን ኤድን በመወከል የቅስቀሳ ሥራ እየሰራ ይገኛል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ጥናት መሰረት በዓለማችን በኤሊኒኖ አየር መዛባት ምክንያት 22 አገራት በድርቅ የተጠቁ ሲሆን 60 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድርቁን ተከትሎ የርሃብ አደጋ አንዣቦባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር እንደምትሽፈን ሮይተርስ ዘግቧል።