ውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአቶ ሀይለማሪያምን ንግግር አስተባበለ

ታህሳስ ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጠ/ሚ/ር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለአልጀዚራ የሰጡትን ቃለ ምልልስ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ ሰጡ።

የኢትዮጲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድረ-ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ የአቶ ሀይለማሪያም ቃለምልልስ በተዛባ መንገድ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን ገልጾ፤ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የተደረገ የፖሊሲ ለውጥ አለመኖሩንም አብራርቷል።

የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔውን ከሰጠበት እ/ኤ/አ  ህዳር 2004 ጀምሮ የኢትዮጲያ መንግስት የያዘው አቋም የማይለወጥና የጸና ሆኖ መቀጠሉን ያመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ፤ አቶ ኃይለማሪያም የተናገሩት በአቶ መለስ ሲገለጽ የቆየና አዲስ ነገር አለመሆኑንም አክሎ ገልጿል።

አቶ ሃይለማሪያም አቶ መለስ ከተናገሩት የተለየ ነገር ያስቀመጡት ወደ አስመራ እሄዳለሁ ማለታቸውን ብቻ ነው ሲልም ማስተባበያው አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ ወር 2002 በኢትዩጲያ ዘመን አቆጣጠር በሚያዚያ 1994 ዓ.ም፣ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያሳለፈበትን እ.ኤ.አ. ህዳር 2004 ዓ.ም. በማለት አዛብቶ አቅርቦታል።