ውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ለግራዚያኒ የሚሰራውን ሀውልት አለም እንዲያወግዘው ጠየቁ

ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የኢትዮጵያውያው የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም የአለማቀፉ ማህበረሰብና የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ እና በሊቢያ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ላደረሰው ግራዚያኒ ሀውልት ለማቆም የሚደረገውን ጥረት እንዲያወግዝ ጠይቀዋል።

ሚ/ሩ ይህን የተናገሩት በሩዋንዳ የደረሰውን ዘር ማጥፋት 19ኛ አመት ለማስታወስ በተጠራ ዝግጅት ላይ ነው። የኢትዮጵያን እና የሊቢያን ዜጎች በግፍ የጨፈጨፈው ግራዚያኒ ሀውልት አይገባውም ብለዋል ሚስትሩ።

የሚኒሰትሩ ንግግር መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም አ/አ ስድስት ኪሎ የካቲት 12 መታሰቢያ ሐውልት እስከ ጣሊያን
ኤምባሲ ሰልፍ በማድረግ በጣሊያን ለፋሽስቱ ግራዚያኒ መናፈሻና ሙዚየም መሰራቱን በመቃወማቸው አለማቀፍ የህግ ባለሙያውን ዶ/ር ያእቆብ ሀይለማርያምን ጨምሮ 38 ያህል ሰዎች በፖሊስ ታስረው ከተፈቱበት ድርጊት ጋር የሚቃረን ሆኖ ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ትችት ሲደርስበት እንደነበር ይታወሳል።