ዊሊያም ዴቪሰን ከሀገር ተባረረ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 29/2010) በኢትዮጵያ የብሉምበርግ ዜና ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪሰን ከሀገር ተባረረ።

ኢትዮጵያን ለቆ ወደ ቋሚ መኖሪያው ለንደን ከተመለሰ በኋላ በማህበራዊ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት የተባረርኩበት ምክንያት ወይንም ጥፋት አልተነገረኝም ሲልም አስታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ ላለፉት 8 አመታት በአዲስ አበባ የብሉምበርግ ዘጋቢ ሆኖ መስራቱን የገለጸው ዊሊያም ዴቪሰን ካለፈው መስከረም ጀምሮ ችግር ሲያጋጥመው መቆየቱን ገልጿል።

የመንግስትና የገዢው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃንን ያህል በዋናነት ለስርአቱ የፕሮፓጋንዳ ስራ ይሰራል በሚል ሲወቀስ የነበረው ዊሊያም ዴቪሰን ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጋር በተያያዘ የሰራው ዘገባ ፍቃዱ እንዳይታደስ በኋላም ከሃገር እንዲባረር ምክንያት እንደሆነ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።

በቢዝነስና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የብሉምበርግ የአዲስ አበባ ዘጋቢ በመሆን ለአመታት በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረገው ዊሊያም ዴቪሰን በመንግስት ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ ከሚደረግላቸው የውጭ ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ ሆኖ መቆየቱንም እነዚሁ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።

በዚህም የተነሳ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዙሪያ የሰራው ዘገባ እንዳስቆጣቸው ተመልክቷል።

በኦሮሚያ ከቀጠለው ሕዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰበት ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ውላችን ካልተከበረ ፋብሪካውን ነቅለን እንወጣለን ማለቱ በብሩምበርግ ተዘግቦ ነበር።

ይህ ዘገባ ኢንቨስትመንትን ይገታል፣የውጭ ምንዛሪ ድርቅም ያስከትላል በሚል በመንግስት ባለስልጣናት ዘንድ ቅሬታ ብሎም ቁጣ መቀስቀሱ ተመልክቷል።

ይህንን ዘገባ ተከትሎም በተለያየ መንገድ ለጋዜጠኛው በመንግስት ሲደረግለት የነበረው ድጋፍ የተቋረጠ ሲሆን የስራ ፈቃዱም እንዳይታደስ ተደርጓል።

በመጨረሻም ትላንት ከሃገር መባረሩን ጋዜጠኛው ራሱ ይፋ አድርጓል።

ከብሉምበርግ ዊሊያም ዴቪሰን በተጨማሪ ለአለም አቀፍ የዜና ወኪሎች ለሚሰሩ ጋዜጠኞች መንግስት ከመኖሪያ ቤት ኪራይ ጀምሮ ልዩ ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ።

ይህም የመንግስትን ገጽታ በመገንበት እንዲተባበሩና ስህተቱን እንዳይዘግቡ ለመከላከል እንደሆነም ተመልክቷል።