ግንቦት ፰ ( ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዞ ከዓመት በላይ በእስር ሲሰቃይ የቆየው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ በቀረበበት የሽብር ክስ ጥፋተኛ ተብሎአል።
በፌስ ቡክ እና ትዊተር ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ምክንያት ለእስር የተዳረገው ዮናታን ተስፋዬ የፀረ ሽብር አዋጁን 652/2001 አንቀፅ 6ን ተላልፈሃል በሚል የጥፋተኝነት ፍርድ ተፈርዶበታል። የፈደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በቅጣት ውሳኔው ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተከሳሽ ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ ”በማሕበራዊ ድረገጾች ላይ ያስተላለፍኳቸው መልእክቶች አመፅ ቀስቃሽ ሳይሆኑ በሕገመንግስቱ የተደነገጉት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴ ነው። ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ በአስተዳደራዊ በደል የመጣ ነው ሲሉ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለፓርላው ሪፖርት አቅርበዋል። ከእኔ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።” ሲል መከራከሪያ ሃሳብ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። በሽብር ሕጉ መሰረት ዮናታን ተስፋዬ ከስድስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ ይችላል ተብሏል።
በተመሳሳይ በኮማንድ ፖስቱ ከጓደኞቹ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አናኒያ ሶሪ ጋር የተያዘው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ ላይ የፍርድ ብያኔ ለመስጠት ለግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል። የጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ለግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።