ወጣት ቱፋ መልካ ጥፋተኛ ተባለ

ወጣት ቱፋ መልካ ጥፋተኛ ተባለ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 01 ቀን 2010 ዓ/ም) በ2009 ዓም ተካሂዶ በነበረውና በርካታ ዜጎች ባለቁበት የኢሬቻ በአል ላይ ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሳ ንግግር አድርገሃል ተብሎ የሽብር ክስ የቀረበበት ቱፋ መልካ ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓም የዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ብሎታል።
ፍርድ ቤቱ ለ55 ሰዎች ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ያደረገው ቱፋ፣ ሟቾቹ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውንና ተጠያቂዎቹ ወታደሮች እንጅ እርሱ አለመሆኑን በመግለጽ የቀረበበትን የጥፋተኝነት ወሳኔ ተቃውሟል። ፈርድ ቤቱም ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት20/2010ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል ትናንት እነ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በቀረበቡትና በውዝግብ በተጠናቀቀው የፍርድ ቤት ውሎ፣ እስረኞች ሰውነታቸው በሚስማር እየተበሳ እንዲሰቃዩ መደረጉን፣ የሃይላንድ ውሃ ብልታቸው ላይ በማንጠልጠል ስቃይ እንደተፈጸመባቸው ፣ ጥፍራቸው እንዲነቀል እንደተደረገና ሌሎችም ስቃዮች እንደተፈጸሙባቸው ፍርድ ቤቱ ማረጋገጡን ገልጿል።