(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 14/2010)
በማዕከላዊ የማሰቃያ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበት ወጣት በፍርድ ቤት ጉዳቱን እንዳያሳይ ተከለከ።
ወጣት ፈዲሳ ጉታ በማዕከላዊ እስር ቤት ከፍተኛ ሰቆቃ የተፈጸመበት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ማዕከላዊን በተመለከተ አነጋጋሪ የሆነ መግለጫ በሰጡበት በዚሁ ሳሞን ነው።
ዳኞች ፈዲሳን ጉዳቱን እንዳያሳይ ከከለከሉት በኋላ የደበደቡህን ክሰሳቸው ማለታቸው ተገልጿል።
ወጣት ፈዲሳ ጉታ የታሰረው ከወለጋ ነው።የተከሰሰው በኦነግ ስም ሲሆን የሽብር ተግባር ለመፈጸም በማቀድና በማሴር በሚል።
የተከሰሰበት ወንጀል እስከ 15 አመታት የሚያስቀጣ ነው።
የፍርድ ቤት የየዕለት ቀጠሮዎችን እየተከታተሉ መረጃ የሚያስተላልፉ አክቲቪስቶች ዛሬም በፈዲሳ ጉታ ቀጠሮ ላይ ተገኝተው ያዩትን የሰሙትን አሰራጭተዋል።
ወጣት ፈዲሳ ከፍተኛ ስቃይ ላይ ነው።ማዕከላዊ የገባው በቅርቡ ሲሆን የሚደርስበት ሰቆቃ በየዕለቱ በፍርድ ቤት ከሚሰማው የታሳሪዎች ስቃይ ጋር ተመሳሳይ ነው።
በማዕከላዊ የደረሰበትን ሰቆቃ ልብሱን በማውለቅ ማሳየት ፈልጎ ነበር።ጥያቄውን ግን ዳኛው አልተቀበሉትም።
ሰቆቃውን የፈጸሙበትን ሰዎች ስም ለመጥቀስ ጠይቆም ነበር።ዳኛው ይህንንም ከልክለዋል።
የደበደቡህን ክሰሳቸው ሲሉም ዳኛው የሹፈት አይነት መልስ ሰተዋል።
ወጣት ፈዲሳ የቀረበበት ክስ ተነቦ የዛሬው ችሎት ተጠናቋል።
በቅርቡም አንድ እስረኛ በማዕከላዊ የተፈጸመበትን ግፍ ገላውን እያሳየ በኤሌክትሪክ ሽቦ የተተለተለ ሰውነቱን እያመለከተ የፍትህ ያለህ ጩህቱን ሲያሰማ በፍርድ ቤት የነበረው ታዳሚ በለቅሶና እሪታ ስሜቱን መቆጣጠር እንዳቃተው መዘገባችን ይታወሳል።
ከጎንደር የታሰረችው ወጣት ንግስት ይርጋ በሕወሃት መርማሪዎች በጉጠት የተነቀሉት ጥፍሮቿን ለማሳየት ፈልጋ መከልከሏም የሚታወስ ነው።
በደረሰበት ድብደባና ስቃይ ምክንያት የተኮላሸውን ብልቱን እየጠቀሰ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ ያለው አበበ ካሴም በዚሁ አጋጣሚ የሚነሳ ነው።
ከሻሸመኔ መሬት ለመሬት ጸጉሯን እየጎተቱ ከደበደቧት በኋላ ጆሮዋ ደምቶ መስማት እንደተሳናት የተሰማው በቅርቡ ነው።
በማዕከላዊ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃ በሕይወት ባሉ ምስክሮች የተጠናቀረ ማስረጃ ቀርቦበት የህወሃትን አገዛዝ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመክሰስ እንደሚቻል የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ባለፈው ረቡዕ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስለማዕከላዊ የተናገሩት ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን አሁንም በየስውር እስር ቤቱ እየተፈጸመ ያለውን የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃ ለማስቆም ርብርብ እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ ነው።
በሌላ በኩል በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኘው የቢላል ሬዲዮ ጋዜጠኛ ካሊድ መሀመድ በደህንነቶች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመበት ታወቀ።
የእስር ቤቱን ዩኒፎርም አለበስክም ተብሎ የተደበደበው ጋዜጠኛ ካሊድ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበትም ለማወቅ ተችሏል።