ሐምሌ ፲፮ (አስራስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በማላዊ ካሮንጎ ከተማ አቅራቢያ 34 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሞክሩ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ማንነቱ ያልታወቀ ማላዋዊ ሕገወጥ ስደተኞችን አስተላላፊ ግለሰብ ”በሙያው የካበተ ልምድ አለኝ፤ከዚህ በፊት ከማላዊ፣ዛምቢያ፣ሞዛምቢክና ዝምባቢዌ ስደተኞችን አሸጋግራለሁ።” በማለት ስደተኞችን አጭበርብሮ በማሳመን 3 ሚልዮን የማላዊ ክዋቻ ተቀብሏቸዋል።የካሮንጋ የስደተኞች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጀርሜህ ፣ ኢትዮጵያውያኑ በካሮንጋ ቺውታ ተራራ አጠገብ እንደደረሱ በጫካ ውስጥ ደብቋቸው ፣ ‘ከዚህ በኋላ የሁለት ሰዓታት ጉዞ ይቀረናል ጠብቁኝ!” በማለት ትቶዋቸው መሰወሩን ገልፀዋል።
ጀርሜህ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ካለምንም ሕጋዊ ቪዛ ማላዊ በመግባታቸው ክስ ይመስረትባቸዋል” ብለዋል።
በሌላ ዜና በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የገቡ 92 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ማክሰኞ ዕለት በኢዞሎ ፍርድ ቤት የአንድ ወር እስራት ተፈረደባቸው።የእስር ጊዜያቸውን ሲጨርሱ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፍርድቤቱ መወሰኑን ዘ ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል።
መንግስት የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ማደጉን በተደጋጋሚ ጊዜ ቢናገርም ኢትዮጵያን ግን አገራቸው ጥለው በባሕርና በየብስ ሕይወታቸው ለአደጋ አጋልጠው መሰደዳቸው የአገሪቱ ዕድገት ለዜጎቹ ሳይሆን ለጥቂቶች የስርዓቱ አባላትና ደጋፊዎች ገፀበረከት መሆኑንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መባባሱን አመላካች ነው ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይከሳሉ።