ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መነሻቸውን በሶማሌላንድ ሳናጋ ግዛት አድርገው በተጨናነቀ ጀልባ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ባሕር አቆራርጠው ወደ የመንና የገልፍ አገራት ለመግባት ሲጓዙ ከነበሩት ኢትዮጵያዊያንና ሶማሊያዊያን ዜጎች ውስጥ አብዛኞቹ መሞታቸውንና ከሟቾቹ ውስጥ 122 የሚሆኑት አስከሬናቸው በባህር ዳርቻዎች መገኘቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
ከአደጋው ሕይወታቸው የተረፈ 80 ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውንና በድንበር ጠባቂዎች መያዛቸውን ዘገባው ገልፆ ፣ ከተያዙት ውስጥ አብዛኞቹ በምግብ እጦትና በውሃ ጥም ድርቀት ሳቢያ አሳሳቢ የጤና እክሎች ያሉባቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በበርበራ የወደብ ዳርቻ የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑም ሆርስ ሚዲያ አክሎ ዘግቧል።
የሳናጋ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አህመድ አብዲ ፋላይ ሶስት በአካባቢው ተራራ ጥግ ተደብቀው የነበሩ ጀልባዎች መያዛቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በአራቱም የዓለም ማእዘናት መፍለሳቸውን አላቋረጡም። ገዥው መንግስት ኤኮኖሚያዊ ለውጥ አምጥቻለው እያለ ሌት ከቀን ቢናገርም፣ ዜጎችን ከሶማሊያና በጦርነት ከምትታመሰው የመን ስደት እንኳን ያልታደገ ለውጥ መሆኑ የሚያሳየው ወጣቶች ምን ያህል በአገራቸው ተስፋ ማጣታቸውን አመላካች መሆኑን እንደሚያሳይ ታዛቢዎች ይገልጻሉ።