ሰኔ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው በ2004 በጀት አመት 10 ወራት ውስጥ ብቻ 140 ሺ ዜጎች ሥራ ፍለጋ ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት መጓዛቸውን ይህ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ329 በመቶ ማሻቀቡን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
በትላንትናው ዕለት በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ይፋ የሆነው ይህው ጥናት እንደሚያመለክተው በህገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡት ዜጎች ቁጥር በአስደንጋጭ መልኩ ማሻቀቡን የጠቆመ ሲሆን ተጓዦችም በአብዛኛው ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል ገጠራማ አካባቢዎችና ከተሞች የፈለሱ ናቸው።
እነዚህ ዜጎች በሱዳን፤ በጂቡቲ፤ በየመንና በሶማሌ ላንድ በማቋረጥ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚጓዙት ወደ ኳታር፤ ሳዑዲ አረቢያ፤ ኦማን፤ ቤይሩት፣ ዮርዳኖስና የመሳሰሉት አገራት ነው፡፡
የአብዛኛዎቹ ተጓዦች የዕድሜ ክልልም ከ15 እስከ 30 አመት መሆኑን የጥናቱ ግኝት ያስረዳል፡፡
ህገወጥ ደላሎቹ ወደ አረብ ሀገራት ለሚያቀኑ ዜጎች ከ8 እስከ 15 ሺ ብር፣ ለግብፅ ከ30 እስከ 50 ሺ ብር ፣ለደቡብ አፍሪካ ደግሞ እስከ 100 ሺ ብር ድረሰ እንደሚያስከፍሉ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የግብፅ፤የጅቡቲ የሱዳንና የሌሎች ሀገራት ዜጎችም በህገወጥ የቪዛ ንግድ ሰራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቅሶአል፡፡
በዚህ ላይ ከህገወጥ ደላሎች በተጨማሪ አንዳንድ ህጋዊ ኤጀንሲዎችም በህጋዊነት ሽፋን ከፍተኛ ወንጀል ውስጥ መግባታቸውንም ጥናቱ አመልክቶአል፡፡
በያዝነው አመት 691 የሚሆኑ ቤተሰቦቻችን ያሉበትን አድራሻ ማወቅ አልቻለንም ያሉ ቤተሰቦች ወደ መንግስት ቀርበው በተደጋጋሚ ማመልከታቸውንና በተደጋጋሚ ማጣራት ቢደረግም የእነዚህ ዜጎች ሁኔታ ግልጽ ያለ መረጃ ሊገኝ አለመቻሉን በያዝነው አመት ብቻም ከ190 በላይ የሚሆኑ ኢትየጵያውያን በተለያዩ የአረብ ሀገራት ግድያ ተፈፅሞባቸው ወደ ሀገር ውስጥ አስክሬናቸው እንዲመጣና ባሉበት እንዲቀበሩ መደረጉንም ያትታል።
ይህም ወደ አረብ ሀገራት እየተደረገ ያለው ጉዞ ከጥቅሙ ይልቅ ምን ያህል ችግሩ እየሰፋና ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ይላል ጥናቱ።
በህጋዊም ይሁን በህወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት የሚያቀኑት ዜጎች ለስራ በሚሄዱባቸው ሀገራት የሚያደርጉት የስራ ውል ደህንነታቸው የሚያስጠበቅ ካለመሆኑም በላይ ችግር ሲያጋጥማቸው እንኳን የሚሸሹበት አጋጣሚ አለመኖሩንም ያነሳል።
አሰሪዎች በዜጎቻችን ላይ የሚያደርሱት በደል ከስነልቦና አንጻር ማግለል፤ መሳደብ፤ ትርፈራፊ ምግብ መስጠት፤ ምቹ የመኝታ ክፍል አለመስጠትና ብዙ ሰአት ማሰራትን ሲያነሳ ከአካላዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ደግሞ መደብደብ፤ አስገደዶ መድፈርና የተለያዩ የአካል ስርቆት መፈፀም ይጠቀሳል።
በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ በሚመለከታቸው አካላት ለዜጎች የግንዛቤ ማስፋት ሰራዎችን በሚጠበቀው ደረጃ መስራት አለመቻላቸውም ለችግሩ መባባስ የራሱን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተገልጿል።
በተለያዩ የዓረብ አገራት ኢትዮጵያዊያን ችግር ሲደርሰባቸው በየአገሩ ያሉት ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ለምን ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደማይሰጡ በጥናቱ አልተካተተም፡፡በኢትዮጽያ በአሁኑ ሰዓት 235 ያህል ህጋዊ ኤጀንሲዎች ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡
ለአቶ መለስ ጽህፈት ቤት የቀረበው ይህ ጥናት ዋና ዋና የሚባሉትን ችግሮች አልጠቀሰም። መንግስት ሰው ጉልበት ኤክስፖርት ማድረግ በሚለው አዲሱ ፖሊሲ ከዜጎች ሽያጭ ከፍተኛ ገንዘብ እየተቀበለ በተዘዋዋሪ መንገድ የባሪያ ንግድ እያካሄደ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ መንግስታዊ ያልሆነ ደርጅት ሀላፊ ተናግረዋል።
መንግስት በአገር ውስጥ ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከስራ አጥነት ጋር በተያያዘ ያለውን አስፈሪ ድባብ ለመግፈፍ የሚፈልገው ወጣቶች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ በተዘዋዋሪ መንገድ እያበረታታ ነው የሚሉት ሃለፊው በቅርቡ ደግሞ ሰው ጉልበት ወደ ውጭ እንልካለን የሚል አዲስ ፖሊሲ በመንደፍ ዜጎች በገፍ እንዲሰደዱ እያበረታታ ነው ሲሉ ይከሳሉ። መንግስት ጧት ማታ ስለዲያስፖራው ገቢ፣ ለዲያስፖራው ስለሚሰጠው መሬትና ዲያስፖራው ስለሰራቸው ቤቶችና ስለገዙዋቸው መኪኖች ፣ ስለሚኖረው የተንደላቀቀ ኑሮ በቴሌቪዥን ደጋግሞ እንዲቀርብ ማድረጉ ወጣቱ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ አገሩን ጥሎ ለመውጣት እያነሳሳው ነው። በመንግስት በኩል ወጣቱ በአገሩ እንዲኮራ፣ አገሩን እንዲለውጥ አይበረታታም የሚሉት ሀላፊው፣ መንግስት ከወጣቱ ቁጣ ለማምለጥ ስደትን እንደ ማስተንፈሻ ቱቦ እየተጠቀመበት ነው፣ ለዚህ ማሳያውም በየቀኑ በኢሚግሬሽን ጽህፈት ቤት ፣ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አረብ አገራትና ሱዳን ኢምባሲዎች ፊት ለፊት የሚኮለኮለውን ወጣት አይቶ መናገር ይችላል ሲሉ አክለዋል። እንደ ሀላፊው ገለጣ በ10 ወራት ውስጥ 140 ሺ ሰዎች ወደ አረብ አገራት ሄደዋል የሚለው ትክክል አለመሆኑን ቁጥሩ ከዚህ ከ ሶስት እስከ አራት እጥፍ ሊደርስ እንደሚችል፣ በመስሪያቤታቸው ጥናት ከ440 ሺ በላይ ዜጎች አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ተናግረዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide