ወደ ውጭ አገር በሚጓዙ የኢህአዴግ ሃላፊዎች ላይ ተቃውሞ ቀረበባቸው

ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2008)

በስራና በግል ጉዳይ ከኢትዮጵያ ወደተለያዩ የአለም ክፍሎች በሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና በተለያዩ ዕርከን ላይ በሚገኙ ሃላፊዎች ላይ የሚካሄደው ተቃውሞ በዚህ በያዝነው ሳምንት ተጠናክሮ መቀጠሉን ለኢሳት የደረሰው ዜና ያስረዳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በስዊዲን ስቶክሆልም ተከታታይ ተቃውሞ ሲገጥማቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ደግሞ ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ፔንታገን ሲቲ ውስጥ ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሳምንቱ መጀመሪያ ማክሰኞ እንዲሁም ትናንት ሃሙስ በስዊድን ርዕሰ መዲና ስቶክሆልም ከኢትዮጵያውያን ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ የጠሩት ስብሰባ መበተኑና መድረኩን ስርዓቱን የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን መቆጣጠራቸው ይታወቃል።

እኤአ ከመጋቢት 11/2011 ጀምሮ ላለፉት 5 አመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙትና ለዩኒቨርስቲው መዳከም ለስርዓቱ በመሳሪያነት እየተጠቀሙ ነው የሚባሉት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ በዋሽንግተን አቅራቢያ ፔንታገን ሲቲ ኮስኮ በተባለ መደብር ውስጥ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

በዚህ የጅምላና የችርቻሮ መደብር ውስጥ አልባሳት በመምረጥ ላይ ሳሉ የዲሲ ግብረሃይል በሚባለው ቡድን ዕይታ ውስጥ የገቡት ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ፣ ዩኒቨርስቲውን በማዳከም ለስርዓቱ ተባባሪ ሰለመሆናቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና የመሳሰሉ ምሁራንን ከዩኒቨርስቲው በማባረር የተጫወቱትን ሚና አክቲቪስቱ መኮንን ጌታቸው ሲቃወማቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ለኢሳት ደሶታል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ ለንባብ ባበቁትና “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ህልሞች” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት መጽሃፍ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በታሪክ የወደቁበትና የካድሬዎች መፈንጫ የሆነበት ዘመን ላይ መድረሱን ጽፈዋል።

ዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ጊዜ “ያሁኑ ይባስ” በሚል የገልጹት ዶ/ር መረራ፣ “በአጭሩ በዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ስር የካድሬዎች አስተዳደር የሰፈነ ይመስላል፣ ከንጉሱና ከደርግ ዘመን ጋር እንኳን ሲወዳደር የአካዳሚ ነጻነቱ ወደ ጠርዝ የተገፉበት ዘመን ላይ ደርሰናል፣ ሹመት፣ ሽልማት ዕድገት ወዘተ በፖለቲካ መነጽር እየታየ ነው” ሲሉ ዶ/ር መረራ በመጽሃፋቸው ገልጸዋል።

በአፍርካ ውስጥ በዕድሜውም በደረጃውም በቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዱ የሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአፍሪካ ውስጥ ያለው ደረጃም በከፍተኛ ደርጃ እየወረደ መምጣቱን ጥናቶች አመልክተዋል።

ፎር ኢንተርናሽናል ኮሌጅስ ኤንድ ዩኒቨርስቲስ የተባለ ተቋም በ2015 ባወጣው የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ደረጃ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያለበት ደረጃ 40ኛ ሲሆን፣ ሌላ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ከመጀመሪያዎቹ መቶ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም።

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን በቅርቡ ባወጣው የ2015 የአፍሪካ የመልካም አስተዳደር ጥናት በትምህርት ስርጭትና ጥራት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከመጨረሻ 6ኛ መሆንዋን ማስፈርም ይታወሳል።