ኢሳት (መስከረም 16 ፥ 2009)
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባትን አለማግኘቱን ተከትሎ ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ ተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመደቡ ተማሪዎች የምደባ ቦታን ለመቀየር በትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉን ለኢሳት ገለጡ።
ይኸው በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በመፈጸም ላይ ይገኛል ያሉት ሙስና ከትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላቸው ደላሎችና ለዚሁ ተብለው በተቋቋሙ ድረ-ገጾች አማካኝነት መሆኑንም ምንጮች አስረድተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ከተማሪዎች እየቀረበ ባለው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጦ፣ ዩኒቨ-ኮሌጅ የተሰኘ ድረገፅ ከ3 ሺ በላይ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ ዝውውር እፈጽማለሁ በማለት ምዝገባ ማካሄዱን ገልጿል።
ይሁንና የትምህርት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ምዝገባን አካሄዷል ቢልም፣ በድረ-ገፁ ላይ ስለተወሰደ እርምጃ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ሙስና መበራከቱን ለኢሳት ያስታወቁት ምንጮች አንድ ተማሪ ወደሚፈልገው ዩኒቨርስቲ ለመቀየር እስከ 10 ሺ ብር እንደሚጠየቅ አስረድተዋል።
ለወራት በኦሮሚያ ክልል የዘለቀው እና በሃምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እንዳይጓዙ ስጋትን መፍጠሩን መምህራንና ወላጆች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
በክልሎቹ ያለው አለመረጋጋት በተማሪዎች ዘንድ የፈጠረውን ስጋት ተከትሎ የትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ከመምህራን እና ወላጆች ጋር ሃገር አቀፍ የውይይት መድረክን እያካሄደ ይገኛል።
ይሁንና፣ በዚሁ መድረክ የተሳተፉ መምህራንና ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው አካላት ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች በዋና አጀንዳነት ባለመነሳታቸው የውይይት መድረኩ የፈታው ችግር አለመሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የትምህርት ሚንስቴር በተያዘው አመት ከ20 በሚበልጡ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ የ100ሺ አካባቢ ተማሪዎችን ምደባ ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ምደባውን ተከትሎ የዝውውር ጥያቄ የሚያቀርቡ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል።
ሚኒስቴሩ በተማሪዎች መካከል የሚደረግን መቀያየርም ሆነ ለውጥ የማይቀበል መሆኑን ቢገልፅም፣ በርካታ ተማሪዎች በዚህ ዝወውር እስከ 10ሺ ብር የሚደርስ ክፍያ እንደሚጠየቁ ምንጮች ለዜና ክፍላችን አስረድተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ህገወጥ ነው ሲል የገለጸው አንድ ድረ-ገፅ ድርጊቱን ዕፈጽማለሁ በማለት የተማሪዎችን ምዝገባ ሲካሄድ መቆየቱን አረጋግጧል።
ይሁንና፣ በድረገፁ ባለቤቶች ላይ በህግ አካላት በኩል ስለተወሰደ እርምጃ የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ከ3ሺ የሚበልጡት ተማሪዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈሉም ሚኒስትሩ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።