ኢሳት (ኅዳር 22 ፥ 2009)
ሞሮኮ ተሰናባቿ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ሃገሪቱ ዳግም ወደ አባልነት ለመመለስ የያዘችውን ሂደት አጓተዋል ስትል ይፋዊ ቅሬታን አቀረበች።
የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል ሞሮኮ ሃገሪቱ ግዛቴ ናት ለምትላትው የሰሃራዊ ሪፐብሊክ ዕውቅና መሰጠቱን ተከትሎ ከ32 አመት በኋላ ከአህጉራዊ ድርጅት አባልነት እራሷን ማግለሏ ይታወሳል።
ይሁንና የሞሮኮ ባለስልጣናት በሰሃራዊ ሪፐብሊክ ያላቸውን አቋም ሳይለወጡ ዳግም ወደ አፍርካ ህብረት ለመመለስ ጥያቄን አቅርበው የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ድምፅ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን ያወጣው የሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃገሪቱ ያቀረበችውን ጥያቄ በኮሚሽኑ ሊቀመንንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ምክንያት እንዲጓተት ተደርጓል ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ቅሬታን አቅርቧል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጉዳዩ ዙሪያ ለአባል ሃገራት ድምጽ የማሰባሰብ ሂደትን ማከናወን ቢኖርበትም ተሰናባቿ ሊቀመንበር ሂደቱን ሆን ብለው እንዲዘገይ አድርገዋል ሲል የሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ቪኦኤ እንግሊዝኛው ክፍል ሃሙስ ዘግቧል።
“የህብረቱ ሊቀመንበር ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ በመክተት፣ የህብረቱን ደንቦች በአግባቡ ተግባራዊ አላደረጉም” ስትል ሞሮኮ ቅሬታዋን አቅርባለች።
ከአንድ ወር በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የህብረቱ ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የሞሮኮ ጥያቄ ድምፅ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። የሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ 54ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት መካከል 36ቱ ለሰሃራዊ ሪፐብሊክ ዕውቅናን የማይሰጡ ናቸው ሲል ይገልጻል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ምዕራባውያን ሃገራት ለሰሃራዊ አረብ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዕውቅናን አልሰጡም። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በሞሮኮ ስለቀረበበት ቅሬታ የሰጠው ምላሽ የለም።
የሞሮኮ ንጉስ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ሃገራቸው ዳግም ወደ ህብረቱ ለመመለስ ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማግባባት ስራ ሲያካሄዱ እንደነበር ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሞሮኮ ወደ አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አባልነት ለመመለስ ለያዘቸው እንቅስቃሴ ሃገራቸው ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል የገቡ ሲሆን፣ ሞሮሞ የተገባላትን ቃል ተከትሎ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ስምምነት ፈርማለች።