ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት ጨምሯል

ግንቦት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህወሃት/ ኢህአዴግ የ25ኛ አመት በአሉን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በማውጣት ድል ባለ ድግስ ባከበረ ማግስት ዜጎች ቀያቸውን እየጣሉ ወደ አዲስ አበባ በመሰደድ ላይ ናቸው። አዲስ አበባ መድረስ ያልቻሉት ደግሞ በዋና ዋና የክልል ከተሞች በብዛት እየተሰደዱና በልመና ህልውናቸውን ለማቆየት እየጣሩ ነው። ዝርዝር አለን።

ህወሃት መራሹ አስተዳደር በኢትዮጵያ ታምራዊ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ማስገንዘቡን ይናገራል። አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት በመንግስት የሚሰጠውን የእድገት አሃዝ መረጃ እንደወረደ ያቀርቡታል። አልፎ አልፎ በቁጥር ልዩነት ቢኖርም፣ የኢትዮጵያ እድገት ተአምራዊ መሆኑንና ለአፍሪካም በምሳሌነት የሚቀርብ መሆኑን ይገልጻሉ። በእርግጥም በአዲስ አበባ እና በዋና ዋና ከተሞች ግንባታዎች ይካሄዳሉ። ከውጭ አገር የመጡ ኢትዮጵያውያን ሰርተው ለዘመናት ያጠራቀሙትን ገንዘብ በመያዝ ወይም ከባንክ በመበደር ህንጻዎችን ይገነባሉ። በአገር ውስጥ የሚኖሩ በተለይም ባለስልጣናትና ከባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ያላቸው  ሰዎች በተለያዩ የሙስና መንገዶች የዘረፉትን ገንዘብ በመጠቀም እነሱም ዘመናዊ ህንጻዎችን ይገነባሉ።  በሙስና የሚገነቡት ቤቶች ለመስራት በሚል በአዲስ አበባ ብቻ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በየክልሎች የተፈናቀለው ሲጨመርበት አሃዙ ወደ ሚሊዮን ያሻቅባል።

በኢትዮጵያ የሚታየው እድገት አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ አለማድረጉ በዚህ አመት የተከሰተው ረሃብ በቂ ምስክር መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። 20 ሚሊዮን ዜጎች ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል። የአለማቀፉ ማህበረሰብ ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ በርካታ ዜጎች ከሞት መትረፋቸው ቢነገርም፣ ችግሩ ግን አሁንም እንዳለ ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው። መንግስት ከገጠር የሚሰደዱ ዜጎች የአገሪቱን ገጽታ ያበላሻሉ በሚል በተለይም የውጭ አገር ዜጎች እንዲያዩዋቸው በሚፈለጉ ቦታዎች ፣ በልመና የሚተዳደሩ ዜጎች እንዳይታዩ ለማድረግ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ቢሆንም ፣ ዜጎች የሚደርስባቸውን ችግር ተቋቁመው መጽዋት መለመናቸውን አላቆሙም። ወኪላችን በቅርቡ ተሰደው ወደ አዲስ አበባ የመጡትን ዜጎች አነጋግሯል። ለስራ የደረሰ ትኩስ ጉልበት ያላቸው ወጣቶች ህይወታቸውን ለማቆየት ወደ አዲስ አበባ መሰደዳቸውን ይናገራሉ። በአካባቢያቸው ስራ ማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ዋና ከተማዋ መሰደድን አማራጭ አድረገውታል። በልግስናው የሚታወቀው የአዲስ አበባ ህዝብ ምጽዋት በመስጠት ወገን ለወገን የሚለውን መርህ ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም፣ ስደቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ አዲስ አበባስ ትችለዋለች ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

የአንድ ህጻን ልጅ እናት የሆነቸው ሴት ደግሞ  አዲስ አበባ ከገባች ሶስተና ሳምንቷ ነው። ትንሽ መሬት አለኝ ትላለች። ድርቅ በመሆኑ ተሰዳለች። ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በሁዋላ ህዝቡ እየረዳቸው መቆየታቸውን ትገልጻለች። አሁን ዝናብ ዘንቧል መባሉን በመስማቷ ወደ ቀየዋ ለመመለስ ፍላጎት አላት።  ትንናት ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን የሚናገሩት እናት ደግሞ ችግሩ ጠንቶባቸው መሰደዳቸውን ይናገራሉ ።  ከመቀሌ ከተሰሰዱ አንድ ወር የሆናቸው እናትም እንዲሁ በቤተክርስቲያን ተጠልለው ህይወታቸውን በልመና ይገፋሉ፡

የደህንነት ቁጥጥሩ እንደልብ ቀረጻ ለማድረግ ባይቻልም፣ በአዲስ አበባ በልመና የተሰማሩ ህይወት የረሳቻቸው ዜጎች ብዙ የሚናገሩት ታሪክ ይኖራቸዋል። መንግስት በችግር ምክንያት የተሰደደ አንድም ሰው የለም በማለት አሁንም በማስተባበል ላይ ነው። ወኪላችን እንደሚለው ግን በአዲስ አበባ ከውብ ህንጻዎች ስር የሚታዩት አገሪቱ የረሳቻቸውን እጅግ ደሃ ህዝብ ነው።