ኢሳት (ሚያዚያ 4 ፥ 2009)
በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሰደድ ሙከራን የሚያደርጉ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ስደተኞች በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በባርነት በመሸጥ ላይ መሆናቸውን የአለአም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ።
ስደተኞቹን በቁጥጥር ስር የሚያውሉ ታጣቂዎች እና ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞቹን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በአደባባይና በመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች በጨረታ እንደሚሸጧቸው የስደተኛ ድርጅቱ ከድርጊቱ ያመለጡ ሰዎችን ዋቢ በማድረግ ሪፖርት ማስራጨቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአናጢነትና የተለያዩ የእጅ ሙያ ያላቸው ስደተኞች በጨረታ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያወጡ የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅትም ገልጿል።
የናይጀሪያ፣ ጋና፣ ጋምቢያ፣ እና ሴኔጋል ስደተኞች የድርጊቱ ሰለባ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሰዎች በሰሜናዊ የሊቢያ ግዛት በምትገነው የሳብሃ ከተማ መሸጣቸውን ስሙን መግለጽ ያልፈለገውና የድርጊቱ ሰለባ እንደነበር የገለጸው ሴኔጋላዊ ለቢቢሲ አስረድቷል።
የሊቢያ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሴቶችን ጭምር በባርነት በመግዛት ለተለያዩ ጥቃቶችና የጉልበት ስራ እንደሚጠቀሙባቸው ማምለጥ የቻሉ ስደተኞች አስታውቀዋል።
አፍሪካውያን ስደተኞቹን በቁጥጥር ስር የሚያውሉት ታጣቂዎችና የህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በተለይ በቤተሰባቸው በኩል ገንዘብ ሊያገኙባቸው ያልቻሏቸውን ስደተኞች ለዚሁ ድርጊት እያዋሏቸው መሆኑን ተወካዩ አክለው ገልጸዋል። በኒጀር የሚገኙ የስደተኛ ሰራተኞች በሊቢያ ያለው የሰዎች ሽያጭ መኖሩን አረጋግጠው የሳብሃ ከተማ በድርጊቱ የምትታወቅ መሆኗን ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ስደተኞቹን ለተለያዩ የጉልበት ስራ ለመገልገል የሚፈልጉ ደንበኞች በሰው ከ200 እስከ 500 ዶላር ክፍያን እንደሚፈጽሙ ተመልክቷል።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ይህንን አሳዛኝ ድርጊት እንዲታደግ የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ጠይቋል።
በሊቢያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ባለመሆኑ ድርጊቱን መቆጣጠሩ አስቸጋሪ እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይገልጻሉ። የቀድሞ የሃገሪቱ መሪ ሞሃመድ ጋዳፊ ከስልጣን መወገድን ተከትሎ ሊቢያ ለአመታት ባለመረጋጋት ውስጥ ያለች ሲሆን ምስራቃዊ የሊቢያ ግዛት በታጣቂዎች ስር እየተዳደረች ትገኛለች።
በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ያለው የሊቢያ መንግስት ደግሞ መዲናይቱ ትሪፖሊንና አካባቢውን በማስተዳደር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መንግስትና ታጣቂዎችን ለማደራደር ሲያካሄድ የቆየው ጥረት ውጤት አለማምጣቱ ይነገራል።
በምስርቃዊ ሊቢያ ራሱን አይሲስ ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ሰፊ ስፍራን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝም መረጃዎች ያመለክታሉ። በሃገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ መውጣት ሳይችሉ መቅረታቸው ሲገለጽ ቆይቷል።