ኢሳት (ሰኔ 28 ፥ 2008)
የሱዳን መንግስት የሃገሪቱን ግዛት በመጠቀም በሊቢያና ግብፅ ወደ አውሮፓ ለመሰደድ ጥረት የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገለጸ።
ባለፈው ወር ብቻ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ከ300 በላይ ስደተኞች ሱዳንን ከሊቢያ በሚያዋስናት የሃገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኮማንደር የሆኑት ጄኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ለሱዳን ትሪቢዮን ጋዜጣ አስታውቀዋል።
የስደተኞቹ ቁጥር መበራከትን ተከትሎ የሱዳን መንግስት በሰሜን እና ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ የበረሃ አካባቢዎች ላይ የቁጥጥር ዘመቻ መክፈቱን ጀኔራሉ ገልጸዋል።
ሱዳን ከሊቢያ ጋር በምትዋሰንበት የሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል በአሁኑ ሰዓት ለዘመቻው ሲባል ዝግ መደረጉንና የስደተኞቹ ጉዳይ ለሃገራቸው አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጄኔራል ሞሃመድ ማምዳን ለሱዳን መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደሃገራቸው በመግባት ላይ መሆኑን የተናገሩት የሱዳኑ ጄኔራል የአውሮፓ ህብረት ሱዳን ስደተኞችን ለመቆጣጠር ለምታደርገው ጥረት በቅርቡ የ100 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።
የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት (IOM) እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በርካታ ኢትዮጵያውያን በጎረቤት ሱዳን እና ጅቡቲ በኩል በማድረግ ከሃገር በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ባለፈው ሳምንት በስደተኞች ዙሪያ አመታዊ ሪፖርቱን ያወጣው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጎረቤት ሱዳንና ጅቡቲ በርካታ ስደተኞች የሚያቋርጡባቸው ሃገራት ሆነው መምጣታቸውን ይፋ አድርጓል።
የሪፖርቱ ይፋ መደረግ ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሰጠችው ሱዳን የሃገሯን ግዛት እያቋረጡ ወደ ሊቢያና ግብፅ በመሰደድ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የሌላ አገር ዜጎች ጉዳይ አሳስቧት እንደሚገኝ ገልጻለች።
ከኢትዮጵያ የሚደረገው የሰዎች ስደት መጨመርን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት ከወራት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር ያካሄዱ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሱዳን፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመንና ሌሎች ሃገራት እንደሚገኙ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ወደሱዳን የሚሰደዱ ሰዎችን ለመቆጣጠር በሚል በሁመራ ከተማ ዙሪያ ቁጥጥር ቢያደርግም የስደተኞቹ ጉዞ አለመቋረጡን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።