ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2009)
ከተለያዩ ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በተጠቃሚ እጆች የሚገኙ ወደ አራት ሚሊዮን አካባቢ የእጅ ስልኮች (ሞባይሎች) አገልግሎት እንዳይሰጡ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ።
የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከወራት በፊት በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ አዲስ የመመዝገቢያ ስርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ መመሪያ አውጥቶ የነበር ሲሆን፣ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ ሞባይሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በዚሁ መመሪያ ተደንግጓል።
አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግና ከጥቅም ውጭ የሚሆኑትን አራት ሚሊዮን ስልኮች እንዴት መተካት አለባቸው በሚለው ጉዳት በኢትዮ-ቴሌኮምና በሃገር ውስጥ የሞባይል አምራቾች መካከል ድርድር ቢካሄድም መግባባት ሳይደረስ መቅረቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የእጅ ስልካቸው ከጥቅም ውጭ ለሚሆንባቸው ደንበኞች ተቀያሪ ስልኮች በሚሰጡበት ጊዜ የተቀያሪ ስልኮችን ወጪን ማን ይሸፍነው የሚለው ጉዳይ አለመግባባት ላለመደረሱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ታውቋል።
ኢትዮቴሌኮም 55 በመቶ ወጪውን እንዲሸፍን አምራቾች ደግሞ ቀሪውን ወጪ እንዲሸፍኑ የሚል አማራጭ እንደቀረበ ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል።
ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ አሁንም ድረስ መግባባት ያልተደረሰ ሲሆን፣ ደንበኞች የያዟቸው ስልኮች አይነት ግምት ውስጥ ሳይገባ በሌላ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እንዲቀይሩ እንደሚደረግ ለመረዳት ተችሏል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሞባይል ባለቤቶች አማራጭ ያልቀረበላቸው ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከውጭ ገብተዋል የተባሉት የእጅ ስልኮች ዘመናዊ ስልኮች መሆናቸው ይነገራል።
አዲሱ የመንግስት መመሪያ ከመጽደቁ በፊት መዘጋጀት ያለብን ብዙ ጉዳዮች አሉ ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀሰ የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አንድ የስራ ሃላፊ ለጋዜጣው አስረድተዋል።
ኢትዮ-ቴለኮም ከወራት በፊት የእጅ ስልኮችን ለመመዝገብ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ እንደሚደረግ በገለጸ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዕርምጃው የተጠቃሚዎችን መረጃ ለመሰለልና ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የሞባይል ስልክ አገልግሎት በሃገሪቱ ከ18 አመት በፊት በ36ሺ ደንበኞች በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ ወደ 47 ሚሊዮን አካባቢ እንደደረሰ መንግስት ይገልጻል። ይህ ቁጥር ከአለም ሃገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑንም መረዳት ተችሏል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሞባይል ቴሌፎን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአለም የመጨረሻዎቹ 10 አገራት እንደሆነችም ተመልክቷል።