ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2009)
የታንዛኒያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ስጋት እየሆነ መምጣቱን ረቡዕ አስታወቁ።
በዚሁ ድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ 13 ኢትዮጵያውያን ሰኞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ታንዛኒያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን አክለው ገልጸዋል። ከአንድ ወር በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል የተባሉ 83 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ይታወሳል።
የኪሊማንጃሮ አስተዳደር (ግዛት) ፖሊስ ኮማንደር የሆኑት ዊልብሮድ ሙታፋንግዋ 13ቱ ኢትዮጵያዊያን ታንዛኒያ ከኬንያ በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ በጸጥታ ሃይሎች ሊያዙ መቻላቸውን እንደገለጹ ሺንሁአ ዘግቧል።
ከኬንያ በኩል ወደ ታንዛኒያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን እና የሌላ ሃገራት ስደተኞች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ሃገሪቱ በድንበር አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥር በቅርቡ መዘርጋቷ ታውቋል።
ይሁንና፣ አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ እንዲሁም የኬንያ ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ለመግባት ጥረት እንደሚያደርጉ የፖሊስ ኮማንደሩ አስረድተዋል።
የታንዛኒያ መንግስት ባለፈው አመት ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ ከ30 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ኬንያ ድንበር እንዲሰፍሩ ማድረጉን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው።
እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ወደ ኬንያ ይግቡ አይግቡ የሃገሪቱ ባለስልጣናት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ታንዛኒያ በ13ቱ ኢትዮጵያውያን ላይ የምትወስደው ዕርምጃ ከመግለጽ ተቆጥባለች።
የኪሊማንጃሮ ግዛት የኢሚግሬሽን ሃላፊ የሆኑት ኢብሮሲ ማኩንጉ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገሪቱ በመግባት በመምህርነት የሚሰጡ ኬንያውያን ለማደን በድንበር ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በመስሪያ ቤታቸው ይህንኑ ቁጥጥር ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዳለ ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ሊገኙ መቻላቸውንም አክለው አስረድተዋል።
በህገወጥ መንገድ በታንዛኒያ በመምህርነት የሚያገለግሉ ኬንያውያን የማስተማር ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በየዕለቱ ወደ ኬንያ እንደሚመለሱ ሃላፌው ለሺንሁአ ተናግረዋል።