ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሕገወጥ መንገድ ድንበር ቆራርጠው በማላዊ የድንበር ከተማ ካሮንጋ በኩል በአንድ ተሽከርካሪ ላይ ተጭነው የነበሩ 26 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በድንበር ፖሊስ መያዛቸውን የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎችን ጭኖ በፍጥነት ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ ከቺቲፓ ወደ ካሮንጋ አውራጃ የሚወስደውን M1 አውራ ጎዳና ይዘው ሲጓዙ ነበር። የድንበር ፖሊሶችን መምጣት በማየት መንገዳቸውን ቀይረው በካሮንጋ አየር ማረፊያ አድርገው ወደ ካቲሊ ሲያቀኑ ፖሊስ መንገዱን በመዝጋት በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የካሮጋ ፖሊስ ጣቢያ ምክትል አዛዥ የሆኑት ጆርጅ ሚልዋ አስታውቀዋል።
ጆርጅ ሚልዋ አክለውም ”የፖሊስ አባላት መኪናውን ሲከታተል በነበረበት ወቅት የመኪናው አሽከርካሪ መኪናውን በማቆም ከኢትዮጵያዊያን ስደተኞቹ ጋር በአቅራቢያቸው በሚገኝ ደን ውስጥ ተደብቀዋል።”ብለዋል::
ፖሊስ ክትትሉን አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያዊያኑን ስደተኞች እና የመኪናውን አሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች እድሜያቸው ከ25 እስከ 35 ዓመት የሚሆናቸው ወጣቶች ናቸው።
የመኪናው አሽከርካሪን ጨምሮ ሃያ ስድስቱም ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ በመግባታቸው ክስ እንደሚመሰረትባቸው እና በአሁኑ ወቅትም በእስር ቤት እንደሚገኙ ኒያሳ ታይምስ ዘግቧል።