ወደ መሃል ሐገር የጦር መሳሪያዎች በመግባት ላይ ናቸው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 19/2010)ወደ መሃል ሐገር በከፍተኛ ደረጃ የጦር መሳሪያዎች በመግባት ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዚህም ሳቢያ መሳሪያ ግዥና ሽያጭ ቀጥሏል።

ይህንን ለመግታትና በተለያዩ ቦታዎች የተከማቹ መሳሪያዎችን ለመያዝ የቀጠና 5 ኮማንድ ፖስት በአማራ ክልል አሰሳ ላይ መሆኑም ተመልክቷል።

በሕወሃቱ የጦር አዛዥ በሜጀር ጄኔራል ፍስሃ ኪዳኑ የሚመራው የቀጠና 5 ኮማንድ ፖስት በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ መሳሪያዎችን ለማስቆም በሚል በአማራ ክልል  ነዋሪዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረገው ጥረት ተቃውሞና የአጸፋ ምላሽ እንደገጠመው ሲገለጽ ቆይቷል።

መሳሪያ የማስፈታቱ ርምጃ የተጠበቀውን ውጤት ባለማምጣቱና ያልተሰበ ሁኔታ እየጋበዘ በመገኘቱ ሕገ ወጥ መሳሪያዎችን ለመያዝ በሚል አሰሳ ተጀምሯል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው በተደረገው አሰሳ በባህርዳር ከተማ ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ከ15 በላይ መሳሪያዎችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥይቶች ተገኝተዋል።

በባህር ዳር ከተማ በግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ስሙ ካልተገለጸ ግለሰብ መኖሪያ ቤት 14 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣3 ሽጉጥ እንዲሁም 267 የመትረየስ፣የክላሽና የሽጉጥ ጥይት መያዙንም የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እነዚህ 17 የጦር መሳሪያዎች ከአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በእርግጥ ተገኝተዋልን የሚለውን ከነጻ ምንጭ ማረጋገጥ አልተቻለም።

ሆኖም መንግስት በተቀናቃኝነት የሚፈርጃቸውን ግለሰቦች ወንጀሎ ለማሰር የጦር መሳሪያዎች፣ፈንጆዎችና መሰል ቁሶች በግለሰቦች ቤት እንደተገኙ በማድረግ ንጹሃንን ሲያስር መቆየቱን ሰለባዎቹ ሲናገሩ ቆይተዋል።የመብት ተከራካሪዎችም በዚህ ዙሪያ የማረጋገጫ መግለጫ ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሌላ የጦር መሳሪያ በማሻሻጥ ላይ የነበረ ግለሰብ ከነመሳሪያው በከበባ ይዤዋለሁ ሲልም በቪዲዮ የተደገፈ መግለጫ አሰራጭቷል።