(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 10/2010) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ወደ ሃገር ቤት የሚገባው ሕገወጥ መሳሪያ መጨመሩን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ።
የነዳጅ እቀባ ጥሪውን ተከትሎ ስጋት የገባቸው የነዳጅ ቦቴ ሾፌሮች በአንዳንድ ቦታዎች መቆማቸውንም የኮማንድ ፖስቱ ቃል አቀባይ ለመንግስትና ለፓርቲ መገናኛ ብዙሃን አምነዋል።
የሞያሌ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ የተሰደዱት ደግሞ ኦነግ በነዛው ውዥንብር ነው ሲሉ መናገራቸውም ታውቋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርና የኮማንድ ፖስቱ ቃል አቀባይ አቶ አሰፋ አብዩ በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግላጫቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባው ሕገወጥ መሳሪያ በመጠንም በስፋትም መጨመሩን ገልጸዋል።
ከመሳሪያ ዝውውሩ ጀርባ የኤርትራን መንግስትንም ተጠያቂ አድርገዋል።
ከሕገወጥ መሳሪያ ዝውውሩ በተጨማሪ አሸባሪዎችም በመግባት ላይ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ አሁንም ለመግባት የተዘጋጁና በድንበር ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም አመልክተዋል።
ሕዝቡም በተለይ ድንበር ላይ የሚኖረው ሕዝብ ለመግባት የተዘጋጁትን እንዲከለክሉም የኮማንድ ፖስቱ ቃል አቀባይ ጥሪ አቅርበዋል።
ሳምንት ያህል በዘለቀው የነዳጅ እቀባ ርምጃ ሳቢያ አንዳንድ የቦቴ ሾፌሮች በስጋት ለመቆም መገደዳቸውን አምነዋል።
ሆኖም የነዳጅ እቀባው ተጽእኖ አልነበረውም በማለት ለማስተባበል ሞክረዋል።
ከሞያሌ የተሰደዱትን ኢትዮጵያውያንን በተመለከተም ሰዎቹ የተሰደዱት ኦነግ ባሰራጨው ውዥንብር ተመርተው ነው ማለታቸውም ተመልክቷል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ሕዝባዊ እንደሆነ የተናገሩት የኮማንድ ፖስቱ ቃል አቀባይ አቶ አሰፋ አብዩ ክላሽ ይዞ በሲቪሎች የሚገደል እንደሆነም ተናግረዋል።
በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች የክልል ፖሊስና ሚሊሺያ ጭምር በኮማንድ ፖስቱ ስር በአንድ እዝ እንደሚመራም ተናግረዋል።
ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውሩን ለመግታት በቅርቡ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ሕግ እንደሚወጣም በዚሁ ቃለ ምልልስ ወቅት አንስተዋል።