ወይዘሮ አዜብ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደረሳቸው

መስከረም ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ወይዘሮ  አዜብ ቤተመንግስቱን ለተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያስረክቡ ማስጠንቀቂያ  እንደደረሳቸው ሰንደቅ ዘገበ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከተሾሙ 19ኛ ቀናቸውን የያዙት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደቤተመንግስት እስካሁን መግባት አልቻሉም።

 

በመሆኑም፤ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር  ባለቤትና የህወሓት ሥራአስፈጻሚ አባል የሆኑት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን ለተተኪው ጠ/ሚኒስትር ማስረከብ ባለባቸው ጊዜ ውስጥ ማስረከብ ባለመቻላቸው፤ የማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸው ጋዜጣው አስነብቧል ።

 

ወ/ሮ አዜብ በተተኪነት ሶስት መኖሪያ ቤቶች ተዘጋጅተውላቸው አንዱን መርጠው እንዲገቡ ቢነገራቸውም፤ ባልታወቀ ምክንያት ቤቶቹን ለማየት እንኳን ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ታውቋል።

ወ/ሮ አዜብ ለምን ቤቱን እንደማያስረክቡ የሚሰጡት ምክንያት፤ በቂና አሳማኝ አለመሆኑን የጠቀሱት የጋዜጣው ምንጭ፤ የሰጧቸውን  ምክንያቶች  ግን ከመናገር ተቆጥቧል።

 

< እንደ አሠራሩና ስርዓቱ ቢሆን ኖሮ አቶ ኃይለማርያም በተሾሙበት ዕለት ወደቤተመንግስት መዛወር ነበረባቸው፤  ይህ ግን ከ18 ቀናት ቆይታ በኋላም አልተፈፀመም። ይህም  አነጋጋሪ ሆኗል>ብሏል-የዜናው ምንጪ።

 

በመሆኑም ጠ/ሚኒስትር  ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሚኖሩበት ብስራተገብርዔል አካባቢ ለሥራ ሲወጡና ሲገቡ በትራፊክ መጨናነቅ የአካባቢው ሰዎች እንዳይጉላሉ በማሰብ፤ ማልደው ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው እኩለ ለሊት ላይ ወደ መኖሪያቤታቸው የሚመለሱበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል ተብሏል።

 

ጋዜጣው አቶ ኃይለማርያም የአካባቢ ሰዎችን ነጻነት ላለመጋፋት በሚል ጥብቅ የሆነ አጀባን እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ቢገልጹም ፤ለደህንነታቸው ሲባል ጥበቃው ሊላላቸው አልቻለም ብሏል።

 

በአቶ ኃይለማርያም መኖሪያ ቤት አካባቢ ከወትሮ በተለየ መልኩ ጥበቃው ከመጠናከሩ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደልብ ለመንቀሳቀስ አለመቻላቸው፣ ዘመድ አዝማድም እንደፈለጉ መውጣት መግባት የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩንም ሳምንታዊ ሰንደቅ አመልክቷል።

 

ኢሳት ባለፈው ሳምንት ጉዳዩን አስመልክቶ ባጠናቀረው ሪፖርት፤ ወይዘሮ አዜብ ቤተ-መንግስቱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥራ ሲወጡና ሲገቡ በየጊዜው  መንገዶች እየተዘጉ ህብረተሰቡ በመጉላላት ላይ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።