ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከስልጣን መባረራቸውን ያወቁት በጥበቃ ሰራተኛ ሲታገዱ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)

በቅርቡ ከሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የተባረሩትና ከኤፈርት ሃላፊነታቸው የተነሱት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከስልጣን መባረራቸውን ያወቁት ወደ ቢሮአቸው እንዳይገቡ በጥበቃ ሰራተኛ ሲታገዱ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

በአቶ ስብሃት የሚደገፈው የሕወሃት አመራር ለወይዘሮ አዜብ ደብዳቤ ሳይደርሳቸው ትዕዛዙን ለጥበቃ ሰራተኛው አስቀድሞ ያስተላለፈው ሞራላቸውን ለመንካት እንደሆነም ምንጮቹ ይናገራሉ።

ወይዘሮ አዜብ ተሽከርካሪያቸውንም ጭምር ድንገት ተነጥቀው በሰው መኪና ወደ ቤታቸው መመለሳቸውም ታውቋል።

መቀሌ ሲካሄድ የነበረውን የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውን ተከትሎ ከፓርቲው ስራ አስፈጻሚነት የተባረሩት ወይዘሮ አዜብ መስፍን የሕወሃት የንግድ ተቋም የሆነውን ኤፈርትን እስካለፉት ጥቂት ሳንታት ድረስ ሲመሩ ቆይተው ነበር።

ነገር ግን በቅርቡ ወይዘሮ አዜብ መስፍን ቦሌ መንገድ ሜጋ ሕንጻ ወደሚገኘው ቢሯቸው ሲደርሱ  በጥበቃ ሰራተኛ አማካኝነት ወደ ቤሯቸው እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

በጥበቃ ሰራተኛው አማካኝነት ቁልፍና መኪናቸውን እንዲያስረክቡ የተገደዱት ወይዘሮ አዜብ ጓደኛቸው ጋ ደውለው በጓደኛቸው መኪና ወደ መጡበት መመለሳቸው ታውቋል።

ስልጣኑን የያዘው የሕወሃት ቡድን ወይዘሮ አዜብ መስፍን በኤፈርት ሃላፊነታቸው ወቅት እነ አቶ ስብሃትን ሲወነጅሉ የቆዩበትን እየተበቀላቸው እንደሆነ ታምኖበታል።

በወይዘሮ አዜብ ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ከወይዘሮ አዜብ ጋር ካለው ቅራኔ ባሻገር ሕወሃትን እዚህ ቀውስ ውስጥ የከተተው መለስ ነው በሚል በባለቤታቸው ድርጊት ጭምር ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸውን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።