(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 25/2010) አቶ በረከት ስምዖን ለፍርድ እንዲቀርቡ በአውሮፓ ፓርላማ የፖርቹጋል ተወካይ ወይዘሮ አና ጎሜዝ ጠየቁ።
ህዝብን የጨፈጨፈ ስርዓት ዋነኛው ባለስልጣን የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ይህን ተፈጻሚ እንደሚያደርገው እጠብቃለሁ ብለዋል ወይዘሮ አና ጎሜዝ።
የመለስና የበረከት መንግስት የህዝብን ድምጽ አጭበርብረዋል ያሉት አና ጎሜዝ የአውሮፓ ህብረት እሽሩሩ ማለቱም አበሳጭቶኛል ሲሉ ገልጸዋል።
ሰሞኑን ስለ ወይዘሮ አና ጎሜዝ የተናገሩት አቶ በረከት ስምዖን በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን አገባቸው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
የአቶ በረከትን አዲሱን መጽሀፍ ማንበብ ይፈልጋሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት አና ጎሜዝ የውሸታም ሰው መጽሀፍ ለምን ብዬ አነባለሁ ሲሉ መልሰዋል።
የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየሰጡ ያሉትን አስተያየት ተከትሎ ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል በአውሮፓ ህብረት የፖርቹጋል ተወካይ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
ወይዘሮ አና ጎሜዝ ዋሾና ጨካኝ ሲሉ የገለጿቸው አቶ በረከት ስምኦን ከሳቸው አልፎ ሃገራቸው ፖርቹጋልን ቅኝ ገዢ ሲሉ መሳደባቸው እንዳስቆጣቸው ይናገራሉ።
እንዲያውም አቶ በረከት በገለጹኝ መልኩ ሳይሆን እኔ ማለት ቅኝ ግዛትን መጻረር ፈታኝ በሆነበት ሰአት በሃገሬ ፖርቹጋል የምታወቀው በጸረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎዬ ነው።
የአቶ በረከት ታሪክ እኮ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ይላሉ በኢትዮጵያ በ1997 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ እሳቸውና ጨካኙ ስርአታቸው በዜጎች ላይ ለፈጸሙት ኢ ሰብአዊ ድርጊት ሃገሬ ፖርቹጋልን ነው ተጠያቂ ያደርጋሉ።ይሄን ደሞ መቼም ቢሆን አረሳውም እታገለዋለሁ።
በወቅቱ ከነበሩት የምርጫ ታዛቢዎች እኔ እስከመጨረሻው ያየሁትን ከሌሎች በተለየ መልኩ ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ።
ይሄ ደሞ ትክክል ነው ምክንያቱም ያለሃጢያታቸው በመለስና በበረከት ትዕዛዝ የተገደሉ ሰዎችን ሆስፒታል ድረስ ሔጄ አይቻለሁ።ለዚህ ደሞ የሁሌም ምስክር ነኝ፣ አሁንም ቢሆን አጥብቄ መናገር የምፈልገው ወደፊትም ቢሆን ይህን ጉዳይ እያነሳሁ እታገላለሁ።
ይሄን ስል እኔ ከሃገሪቱም ሆነ ከሕዝቧ ጋ ምንም ችግር የለብኝም እኔ ችግሬ ከአንባገነኖች ጋር ነው ሲሉ በ2007 የተፈጸመውን የምርጫ ውጤት የማጭበርበር ጉዳይ የአምባገነኖቹ ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።
ይህን ጉዳይ የአውሮፓ ህብረትም በቸልታ ያለፈበት ነገር አናዶኛል ያላሉ።
የኢትዮጵያን ታሪክ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው የማውቀው የሚሉት አና ጎሜዝ በ1997 ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ምድር ስረግጥና ህዝቦቿን ሳይ እርግጠኛ የሆንኩት ያ ህዝብ ዲሞክራሲ እንደሚያስፈልገው ነው።
አንድ ነገር ግን በርግጠኝነት መናገር የምፈልገው በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አቶ በረከት ለፈጸሙት ወንጀል ምንም አይነት ማስተባበያ ሊቀመጥለት እንደማይገባ ነው።
ነገር ግን አቶ በረከት በወቅቱ ይህን ወንጀል ለብቻቸው ባይፈጽሙትም እንኳን ይሰሩ ለነበሩት ወንጀሎች ግን ግንባር ቀደሙን ቦታ የሚይዙት አቶ በረከት ስለመሆናቸው በእርግጠኝነት መናግር እችላለሁ።
የአሁኑ ስርአት አቶ በረከትን በቸልታ እንደማያልፋቸውና ተጠያቂ ያደርጋቸዋል የሚል ተስፋ አለኝ ሲሉ ተናግረዋል።
የቀደሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት አስቀድሜ አውቅ ነበር ብለዋል አና ጎሜዝ።
በወቅቱም ለኢሳት መረጃ አቀብለው ነበር ለተባሉትም ሊሆን ይችላል የሚል እጥር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
የአቶ በረከትን አዲሱን መጽሃፍ የማንበብ ፍላጎት አለዎት ወይ የተባሉት አና ጎሜዝ እኔ ብዙ ስራ አለብኝ ብዙ የማነባቸውም መጽሃፎች ስላሉኝ የዚህን ውሸታምና የፕሮፓጋንዳ መፈልፈያ የሆነን ግለሰብ መጽሃፍ ለማንበብ ጊዜ የለኝም ብለዋል።
ወደፊት ምናልባት ስራ ፈት ከሆንኩ ለማንበብ ልሞክር እችላለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።