(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 13/2011)በኢትዮጵያ ባለፉት 27ና 30 አመታት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን እንሰር ብንል የሃገሪቱ እስር ቤት ስለማይበቃ ከተማ መገንባት ይኖርብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
ከሰሞኑ እየታሰሩ ካሉ ሰዎች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ተቃውሞዎችን እንደመብት የተቀበሉት ዶክተር አብይ አህመድ ሕግ ማክበርና ማስከበር ግዴታ መሆኑን ግን በአጽንኦት ተናግረዋል።
የፓርላማ አባላት ውድቅ ያደረጉትን የቋሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫንም በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርምጃቸው ቅሬታ እንደሌላቸውና መብታቸው እንደሆነም በግልጽ አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህምድ ዛሬ ፓርላማ ላይ ቀርበው ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለተነሳባቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ሁሉንም የወንጀል ተጠርጣሪ ለማሰር የሃገሪቱ እስር ቤቶች እንደማይበቁ ተናግረዋል።
ያልተነካካ የለም ያሉት ዶክተር አብይ አህመድ ሁሉንም እንሰር ካልን እስር ቤት ሳይሆን ከተማ መገንባት ይኖርብናል ሲሉም በወንጀል የተጠረጠሩት ብዛት ከፍተኛ መሆኑን አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ወስነናል ሲሉም ተናግረዋል።
እየተወሰደ ካለው የእስራት ርምጃ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ተቃውሞ በተመለከተም መቃወም መብታቸው ነው ሲሉ አክለዋል።
የታገልነውና ለውጡ ያመጣውም ፓርላማውም ክልሎችም እንዲቃወሙ ነው ያሉት ዶክተር አብይ አህመድ ሕግ ማክበርና ማስከበር ግን የሁላችንም ግዴታ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።
ፓርላማው በእጩነት የቀረቡ የቋሚ ኮሚቴ መሪዎችን ውድቅ ማድረጉንም መብቱ እንደሆነና በዚህም አስፈጻሚው አካል ጣልቃ እንደማይገባም ግልጽ አድርገዋል።
ውድቅ ስታደርጉብን ሌላ አማራጭ ለማቅረብ እንገደዳለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምናቀርባቸው ለውጡን የሚደግፉ መሆናቸውን ግን እንድታውቁልን እንፈልጋለን ሲሉም ተደምጠዋል።
ለፓርላማው በቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት የተጠቆሙት አቶ ሞቱማ መቃሳና አቶ አጽብሃ አረጋዊን ፓርላማው ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
በእነሱ ምትክ የቀረቡትን ሁለት እጩዎች ፓርላማው ዛሬ አጽድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ሹመት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተው ከወጡ በኋላ ፓርላማው ውድቅ በተደረጉት ምትክ እንደ አዲስ የቀረቡለትን ሁለት እጩዎች ሹመት አጽድቋል።
ወይዘሮ ለምለም ሐድጎ ለገቢዎች ፋይናንስና በጀት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ሲጸድቅላቸው አቶ ተስፋዬ ዳባ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ተቀብሎ አጽድቋል።