(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2010)
የመከላከያ ሚኒስቴር በመላ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ምልመላ ጀመረ።
በክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር የተጀመረው ወታደራዊ ምልመላ አላማ ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም።
ይህ በመከላከያ ሰራዊቱ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጭምር የተሰራጨው ምልመላ እስከ ጥር መጨረሻ እንደሚዘልቅም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።
እድሜያቸው 18 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወጣቶች እንዲመዘገቡ ጥሪ የሚያቀርበው የመከላከያ ሚኒስቴር ማስታወቂያ በመላ ሀገሪቱ በየቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ምዝገባው እንደሚካሄድም አስታውቋል።
እስከ ጥር 25/2010 የሚካሄደው ምልመላ በተራ ወታደርነት ሰራዊቱን መቀላቀል ለሚፈልጉ ወጣቶች እንደሆነም በይፋ ተገልጿል።
በጄኔራ ሳሞራ የኑስ የሚመራው የሀገሪቱ የመከላከያ ተቋም ይህን ማስታወቂያ ያወጣው በድንገተኛ ይሁን በመደበኛ የታወቀ ነገር የለም።
ሆኖም በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ጥሪ በማድረግ ወታደራዊ ምልመላ ሲካሄድ ከቅርብ አመታት ወዲህ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ተመልክቷል።
ከሶስት ሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል ወታደራዊ ምልመላ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደነበር የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች የተጠበቀውን ያህል ተመልማይ አለመገኘቱንም ያስረዳሉ።
ይህ ከሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል የተጀመረው ወታደራዊ ምልመላ በሌሎች ክልሎች ስለመካሄዱ የታወቀ ነገር የለም።
የግብጽና የሱዳንን ውዝግብ ተከትሎ በአካባቢው የተፈጠረው ውጥረት እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሰጡት መግለጫ የሕወሃት /ኢሕአዴግን መንግስት ስጋት ውስጥ ያስገቡ ክስተቶች ስለመሆናቸው በፖለቲካ ምሁራን ዘንድ እየተገለጸ ይገኛል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ በግንቦት 1990 ወደ ይፋ ጦርነት ካመሩበት ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መንግስታት መካከል ከፍተኛ ቅራኔ መኖሩ ይታወቃል።
አንዱ መንግስት የሌላኛውን ተቃዋሚ በማስጠጋት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውም በይፋ የሚገለጽ ሆኗል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ቡድንን አዲስ አበባ ድረስ በታንክና በመድፍ እየደገፉ ያደረሱት የሻዕቢያ ተዋጊዎች መሆናቸውን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በቅርቡ መግለጻቸው ይታወሳል።