ኳታር በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ተጋበዘች

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2010)በገልፍ ሃገራት ውስጥ በገባው የፖለቲካ ቀውስ  በበርካታዎቹ የአካባቢው  ሃገራት መገለል የገጠማት ኳታር በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ተጋበዘች።

ፋይል

በተለይም ክሳኡዲ አረቢያና ዩናይትድ አረብ ኤምሪት ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ የቆየችው ኳታር  በሳኦዲ አረቢያ በሚካሄደው የአረብ ሊግ ስበሰባ ላይ እንድትገኝ ከሳኡዲ አረቢያ የቀረበውን ግብዣ   የተቀበለች ሲሆን ፣በሚሄዱት ልኡካን ደረጃ ላይ ግን  ውሳኔ  አለማሳለፏምንም አስታውቃለች።

እንዳውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 15 /2018 በሳኡዲ አረቢያ ሪያድ በሚካሄደው የአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ኳታር እንድትገኝ ግብዣውን የላኩት የሳኡዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሃመድ ሰልማን ናቸው።

ልኡል ሞሃመድ ሰልማን በገልፍ ሃገራት  ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ የውጭ ጣልቃግብነትን እንድማይቀበሉ ባለፈው መጋቢት ወር ባሳወቁበት ውቅት ኳታር በአረብ ሊግ ስብሰባ መሳተፍ መብቷ እንደሆነም አመልክተው ነበር።

ሆኖም በኳታር በኩል ይፋዊ ግብዣ ባለመቅረቡ ምላሽ ሳትሰጥ ቆይታለች።

የሰብሰባው ቀን ሲቃረብ  የስብሰባው አስተናጋጅ የሆነችው ሳኦዲ አረቢያ በይፋ ለኳታር ግብዣ ያቀረበች ሲሆን ፣ ኳታርም ዛሬ ረቡዕ  በሰጠችው ይፋዊ ምላሽ በስብሰባው እንድምትገኝ አረጋግጣለች።

በሚሄዱት ልኡካን ደረጃ ላይ ግን  ወሳኔ  አለማሳለፏምንም አስታውቃለች።

ሰብሰባው ከ 10 ቀናት በኋላ እ/አ/አ ሚያዚያ 15 /2018 በሪያድ ሳኦዲ አረቢያ ይካሄዳል።

ኳታር አሸባሪዎችን ትረዳለች እንዲሁም አካባቢውን ለማወክም እየተንቀሳቀሰች ነው በሚል ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ በርካታ የገልፍ ሃገራት ከኳታር ጋር ዲፕሎማሲያዊ  ግኑኝነት አቋርጠዋል።

ከሳውዳረቢያ፣ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ፣ግብጽ እና ባህሬን ከኳታር ጋር የሚያገናኛቸውን የባህር እና የየብስ መገናኛ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሰኔ 2017 ጀምሮ ዘግተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ላለፉት 35 ዓመታት ሲኒማ ማየት የታገደባት ሳኡዲ አረቢያ ዕገዳውን አንስታለች።

በዚህም የመጀመሪያው ሲኒማ ከ 10 ቀን በኋላ በሪያድ እንዲታይ መርሃ ግብር ተይዞለታል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ሲኒማ አፍቃሪዎች ዘንድ እጅግ ዝነኛ የሆነው ብላክ ፓንተር ፊልም  ሚያዚያ 18/2018 ሪያድ ወስጥ  ለዕይታ ይቀርባል።

ሲኒማ ቤቶችን የመገንባቱና የማስፋፋቱ ስራ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።

ሲኒማ ቤቶቹ የጾታ ልዩነት የማይደረግባቸው ሲሆን ፣ስለ ሚቀርቡት ፊልሞች አይነት የተሰጠ መግለጫ የለም ።

የሳውዲው ልኡል መሃመድ ሳልማን  ሴቶች መኪና እንዳይነዱ የተጣለውን ገደብ በማንሳታቸውም ከመጪው ሰኔ ጀምሮ ሴቶች ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ማሽከርከር ይጀምራሉ።