የኮሪያ ዘማቾች አደባባይ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሰየም የኮሪያ ዘማቾች ማህበር ጠየቀ

ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2008)

የኮሪያ ዘማቾች ማህበር በኮሪያ የዘመተውን የኢትዮጵያ ጦር ለማስታወስ በአዲስ አበባ አደባባይ እንዲሰራ ጠየቀ።

በኮሪያ የኢትዮጵያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ መለሰ ተሰማ  ዮንሃፕ “YohanP ለተሰኘው የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት 144 ስኩዌር ሜትር የሚሆን “ቃኘው ኮሪያ” የተባለ አደባባይ በጉለሌ አካባቢ እንዲሰራ ማህበራቸው ግፊት እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቃኘው በኮሪያ እኤአ ከ1950-53 የኮሪያ ጦርነት ጊዜ ወደ ኮርያ የዘመተው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ክንፍ መጠሪያ ነው።

ኢትዮጵያ 6ሺ ጠንካራ ጦር በቀዝቃዛው ጦርነት ስትታመስ ወደነበረችው ኮሪያ ልካ እንደነበር ይታወሳል። የቃኘው አደባባይ መመስረትም ሰዎች የኢትዮጵያ ጦር በኮሪያ የሰራውን ታሪክ እንዲያስታውስና በኮሪያና ኢትዮጵያ መካክል ዘላቂ ወዳጅነት ለመመስረት እንደሚረዳ የኢትዮጵያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ መለሰ ተሰማ ዮንሃፕ ለተባለ ለኮሪያ ዜና ወኪል መናገራቸው ተዘግቧል።

ሆኖም ማህበሩ ለአደባባዩ ማሰሪያ ወደ 8455 የአሜሪካ ዶላር የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ አለመቻሉን ተናግረዋል። አመታዊ የማራቶን ውድድር በቅርቡ በማዘጋጀት ለአደባባይ ማሰሪያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ማህበሩ ማቀዱን በዘገባው ተመልክቷል። በማራቶን ውድድሩም ከኮሪያ ኢምባሲ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያውያንና በኮሪያ ጦርነት የተሳተፉ አገሮች ሰዎች ለመጥራት እንደታቀደ ለማወቅ ተችሏል።