ኮማንደር ዋኘው አዘዘው መንግስትን በመክዳት ወንጀል ተከሰሰ።

ጥር ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰሜን ጎንደር ዞን የጸረሽምቅ ግብረሃይል አዛዥ የሆነው ኮማንደር ዋኘው አዘዘው ከወራት እስር በሁዋላ መንግስትን በመክዳት ወንጀል መከሰሱ ታውቋል።
ኮማንደር ዋኘው በጎንደር በነበረው ህዝባዊ አመጽ ፓርቲውንና መንግስትን በመክዳት ከህዝብ ጋር በመሆን በመንግስት ላይ የተነሳውን አመጽ ለማስቆም ባለመቻሉ፣ መንግስትንና ፓርቲውን ከድቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል። በተለያዩ የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች በአገዛዙ ወታደሮች ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጥቃት ኮማንደር ዋኘው ዋና ተጠያቂ ተደርጓል። ኮማንደሩ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመቀበል ከድርጅቱና ከመንግስት ጎን ከመቆም ይልቅ ከህዝቡ ጋር መቆምን መርጧል በሚል የክስ ቻርጅ ቢዘጋጅለትም፣ ኮማንደሩ ግን ክሱን አልተቀበለውም።
ኮማንደር ዋኘው መርቶት የነበረው የሽምቅ ሃይል በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች ክፉኛ ከተመታና የተወሰነ ሃይልም ከጠፋ በሁዋላ፣ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ ይታወቃል። ኮማንደር ዋኘው ከታሰረ በሁዋላም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች ጥቃታቸውን አላቆሙም። ገዢው ፓርቲ ህዝባዊ እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬዋለሁ ቢልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳትም ሆነ በአካባቢው ያሰፈረውን የወታደር ቁጥር አልቀነሰም።
በሌላ በኩል ከኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ ጋር በተያያዘ ያለምንም ጥያቄ ታስሮ የነበረው የጎንደር ማረሚያ ቤት ሃላፊ ኢንስፔክተር ልጃለም መሰረት ምንም ክስ ሳይመሰረትበት ከእስር ተፍቷል። ኢንስፔክተር ልጃለም ኮ/ል ደመቀ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ወቅት እጁ በካቴና ሳይታሰር እንዲቀርብ አድርግሃል በሚል ሰበብ ቢታሰርም፣ ዋናው ምክንያት ግን ኮሎኔሉን ከጎንደር አውጥቶ ለመውሰድ የተደረገውን ሙከራ በማክሸፉ እንደነበር ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።