ግንቦት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ አስተባባሪ የሆኑትና ከሕዝባዊ አመጹ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ለመከላከል በወሰዱት እርምጃ ተከሰው በጎንደር አንገረብ እስር ቤት የሚገኙት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ ዛሬ ግንቦት በ29 ቀን 2009 ዓ.ም ጎንደር በከፍተኛ ጥበቃ ስር ሆነው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የኮሎኔል ደመቀ ዘውዴን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ምክንያት በማድረግ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አካባቢ መትረየስ በጠመዱ መኪኖች ታጥረው መዋላቸውንና ችሎቱ በሚካሄድበት ወቅት በዚያ አካባቢ እግረኛም ሆነ ባለተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ ተከልክለው መዋላቸውን በስፍራው የሚገኙት የኢሳት ዘጋቢዎች ያደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንዲሁም ታዳሚዎች ብቻ ሳይሆኑ በፍርድ ቤቱ ቀጠሮ የነበራቸው ሌሎች ተከሳሺችና ታሳሪዎች ሁሉ እንዳይገብ ተከልክለው ችሎቱ በዝግ መካሄዱ ታውቋል። አገዛዙ አሁንም ኮሎኔል ደመቀን ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በመውሰድ የማሰቃዬት እቅድ እንዳለው ከማረሚያ ቤት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።