መስከረም ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጎንደር ፍርድ ቤት የቀረቡት በእግት ላይ የሚገኙት ኮ/ል ደመቀ ዛሬ ፍርድ ቤት በድብቅ መቅረባቸው የታወቀ ሲሆን፣ የሽብርተኝነት ክስ እንደተከፈተባቸው ታውቋል።
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስተባባሪ የሆኑት ኮ/ል ደመቀ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ለበርካታ አመታት ያገለገሉ መሆናቸውን እየታወቀ እርሳቸውን በሽብርተኝነት መክሰስ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው በማለት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ተናግረው ነበር።
የህዝቡ ጥያቄ ወደ ጎን ተብሎ ኮ/ል ደመቀ በሽብርተኝነት ወንጀል መከሰሳቸው ትክክል አይደለም፣ ክሱንም እስከመጨረሻው እንቃወማለን በማለት በፍርድ ቤት የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ኮ/ል ደመቀ ለጥቅምት 3 ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጣቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል ግን አሁንም በክልሉ በርካታ ወጣቶች እየተያዙ ነው። በብር ሸለቆና በቤንሻንጉል ጫካዎች ታስረው የሚገኙ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ አንዳንድ ወጣቶች ስቃዩን መቋቋም ተስኖአቸው ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን በየጊዜው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።