(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 19/2011) በቀድሞ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ ኢትዮጵያ ገቡ።
ከ30 አመታት በላይ በስደት የቆዩት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የደርግን ስርአት በመክዳት እንዲሁም የሕወሃት/ኢሕአዴግን መንግስት በመቃወም ላለፉት 30 አመታት ያህል በአሜሪካን ሃገር በጥገኝነት ቆይተዋል።
የደርግን ስርአት በመቃወም ለስራ ከሃገር እንደወጡ በዚያው የቀሩት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የሕወሃት ኢሕአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲወጣ ስርአቱ ኢትዮጵያን እያዳከመና እያፈረሰ ነው በማለት የኢትዮጵያ መድህን የተሰኘ ንቅናቄ መስርተው ሲታገሉ ቆይተዋል።
በኋላም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለረዥም አመታት ድምጻቸው የጠፋው ኮለኔል ጎሹ ወልዴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በይፋ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋሽንግተን በመጡበት ወቅት በኮንቬንሽን ሴንተር የእራት ግብዣ ላይ የተገኙት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ በመድረኩም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተወድሰዋል።
ስርአቱን ከድተው በውጭ ሃገር ሲቀሩ ለውሎ አበል የተሰጣቸውን ገንዘብ መመለሳቸውን በማስታወስ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኮለኔል ጎሹ ወልዴን ያስታወሱት።
ከ32 አመታት በኋላ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተናገሩት ኮለኔል ጎሹ ወልዴ የተጀመረው ለውጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በመሆኑ ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል ብለዋል።
የፓለቲካ ውድድር ውስጥ መግባትም ሆነ ስልጣን የማግኘት ፍላጎት እንደሌላቸውም በግልጽ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሒሩት ዘመነና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።