(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2010)
ኬንያ ወደ ጠፈር ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት መጀመሯ ታወቀ።
የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ኬንያ በመጪው መጋቢት ወር የምታመጥቀው ይህ ሳተላይት የባህር ዳርቻዎቿን ለማሰስና የግብርና ስራዎቿን ለማገዝ እንደሚጠቅማትም ይፋ ሆኗል።
ከአፍሪካ ሃገራት 8ኛ በመሆን ሳተላይት የምታመጥቀው ኬንያ የጃፓን የህዋ ምርምር ማዕከል የሙያ ምክር እንዲሁም በጃፓን መንግስት የ1 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተደርጎለታል።
ነገር ግን ይሄ ድጋፍ ቢደረግለትም ሳተላይቱን ሙሉ በሙሉ ሰርተው በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙት ከናይሮቢ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ኬንያውያን ኢንጂነሮች መሆናቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
በመጪው መጋቢት ወደ አለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ ከተላከ በኋላ በሚያዚያ ይመጥቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የኬንያውያኑ ሳተላይት የኬንያን የባህር ዳርቻዎች ለማሰስና የግብርና ስራዎችን ለማገዝ እንደሚውልም ተመልክቷል።
ከአፍሪካ ሃገራት ኬንያን ጨምሮ 6ቱ ሳተላይታቸውን ወደ ጠፈር አምጥቀዋል።
ግብጽ የዛሬ 20 አመት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1998 የመጠቀችውን ናይል ሳትን ጨምሮ 4 ሳተላይቶች ሲኖሯት ደቡብ አፍሪካ ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1999 የመጠቀችውን ሰንሴት ሳተላይትን ጨምሮ ሁለት ሳተላይቶቿ በጠፈር ላይ ይገኛሉ።
ናይጄሪያ በተመሳሳይ ሁለት ሳተላይቶቿን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2003 ጀምሮ አምጥቃለች።
ከግብጽ፣ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ በተጨማሪ አልጄሪያ፣አንጎላ፣ሞሮኮና ጋና ወደ ጠፈር ሳተላይት ያመጠቁ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።
በአለማችን ሳተላይት ወደ ጠፈር ያመጠቀች ቀዳሚዋ ሀገር የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የአሁኗ ሩሲያ ስትሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1957 ጀምሮ እስከ 1992 1 ሺ 457 ሳተላይቶች አምጥቃለች።
ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1958 ጀምሮ 1252 ሳተላይቶችን ማምጠቋንም መረዳት ተችሏል።