ኬንያ በኢትዮጵያ ድንበር ወታደሮቿን አሰማራች

ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)

ሰሞኑን የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች የኬንያ ድንበርን በመጣስ ሁለት ኬንያውያንን ማገታቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ በድንበር አካባቢ ወታደሮች ማሰማራቷ ተገለጠ።

የኢትዮጵያ ወታደሮች በሳምንት መገባደጃ በሞያሌ አካባቢ በምትገኘው የኬንያዋ ቦሪ መንግደር በወሰዱት በዚሁ እርምጃ ካገቷቸው ሁለት ሲቪሎች በተጨማሪ ጠመንጃዎችን እንዲወስዱ የማሳርቤት ግዛት ኮሚሽነት ሞፋት ካንኪ አስታውቀዋል።

ጉዳዩ በሁለት ሃገራት ዲፕሎማቶች በኩል ክትትል እየተደረገበት ኣንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ድርጊቱን ተከትሎ ኬንያ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይል በአካባቢው ማስፈሯን ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ የምትሰጠውን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ብንሆንም በድንበሩ ዙሪያ ግን የፀጥታ ቁጥጥራችን ተጠናክሯል ሲሉ ካንኪ ለጋዜጣው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች የኦሮሞ ነጻነት ግንባት (ኦነግ) ታጣቂዎች ለመያዝ ነው በሚል በተደጋጋሚ የኬንያን ድንበር በመዝለቅ የሚወሰዱትን ወታደራዊ እርምጃ፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ውጥረት አንግሶ መቆየቱ ይታወሳል።

ከአንድ ወር በፊትም በተባበሩት መንግስታት ተቋማት በኩል የድንበት ውጥረቱ ለመቀነስ በመሪዎች ደረጃ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያና የኬንያ መሪዎች የደረሱትን ይህንኑ ስምምነት ተከትሎም የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበርን በመጣስ በኬንያ እገታን ሲፈጽሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን እርምጃውም በኬንያ በኩል አዲስ ተቃውሞን እንዳስከተለ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የለም።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች የኬንያን ድንበር በመዝለቅ ከለላን በሚፈልጉ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ ህገወጥ እርምጃ ኣየወሰዱ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በዚሁ በኢትዮጵያ ድርጊት በርካታ ስደተኞች ከኬንያ ታፍነው ወደ ኢትዮጵያ መወሰዳቸው መዘገባችን ይታወሳል።