ኢሳት (ሰኔ 16 ፥ 2008)
ኬንያ ከኢትዮጵያ በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ የነዳጅ ክምችት ማግኘቷን ተከትሎ በድንበሩ አካባቢ ከፍተኛ ወታደራዊ ቁጥጥር ልትዘረጋ መሆናን ሃሙስ ይፋ አደረገች።
በድንበሩ አቅራቢያ የሚገኘው የሃገሪቱ የቱርካና ግዛት በኢትዮጵያ ወታደሮች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎችን ለማደን በሚል ተደጋጋሚ ጥቃት ሲካሄድበት መቆየቱ ይታወሳል።
በዚሁ በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ ወታደሮች ሲፈጸሙ የነበሩ ድንበርን የመጣስ ድርጊት በኬንያና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ድርድር ሲካሄድበት መቆየቱን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይሁንና ኬንያ በዚሁ የድንበር አካባቢ የነዳጅ ሃብት ማግኘቷን ተከትሎ ሃገሪቱ በርካታ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያችን በቱርካና ግዛት ልታቋቋም መሆኗን እንደገለጸች ዘ-ስታንዳርድ የተሰኘ የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል።
ኬንያ በሁለቱ ሃገራት ድንበር ዙሪያ የምታቋቁመው ይኸው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ በድንበር አካባቢ ያሉ የጸጥታ ሁኔታዎችን የሚከታተል ሲሆን፣ ሃገሪቱ ከፍተኛ በጀት እንደምትመድብም ይጠበቃል።
የኬንያ የባህር ህይል፣ የአየር ሃይልና የመከላከያ ሰራዊት ሃላፊዎች ሰሞኑን ወደቱርካና ግዛት በማቅናት በክልሉ ሃላፊ ጀስፖት ናኖክ ጋር መምከራቸው ታውቋል።
በቱርካና አካባቢ የተገኘው የነዳጅ ክምችት ከአራት አመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ማምረትን የሚጀምር ሲሆን ሃገሪቱ በአመት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንደምታገኝ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ባለፈው አመት በኢትዮጵያ የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ቢሄራዊ ግንባት ታጣቂዎችን ለማደን በሚል በርካታ ወታደሮችን ወደ ኬንያ ድንበር ማሰማራቷ ይታወሳል።
የኬንያ የቱርካና ግዛት ሃላፊዎች የሃገራቸው ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በኩል የሚፈጸመውን የድንበር መጣስ ድርጊት እልባት እንዲሰጡት ሲሉ ተቃውሞ ሲያቀርቡ መሰንበታቸው ይታወሳል።
በኬንያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በዚህ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከሩ መሆኑን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።