ኢሳት (ታህሳስ 10 ፥ 2009)
ኬንያ በኢትዮጵያ በእስር ላይ እንዳለ ህይወቱ ያለፈ ዜጋውን ጉዳይ ምርመራ እንዲካሄድበት ይፋዊ ጥያቄን አቀረበች።
የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የነበረው ዛካዬ ሙሪኪ ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በእስር ቤት ከቆየ በኋላ ባለፈው ሳምንት ህይወቱ ማለፉንና አስከሬኑ ወደ ኬንያ መጓጓዙን መዘገባችን ይታወሳል።
የሟቹ አስከሬን ወደ ሃገሪቱ መጓዙን ተከትሎም የኬንያ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ አካላት በድርጊቱ ቁጣቸውን ሲገልጹ መሰንበታቸውን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
ከህዝብ የቀረቡ ተቃውሞዎችን ተከትሎ መግለጫን ያወጣው የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዛካዬ ሞት ምክንያት ምርመራ እንዲካሄድበት ከኢትዮጵያ ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የኢንፎርሜንሽ ቴክኖሎጂ ባለሙያ የነበረው ኬንያዊ በአንድ የኬንያ ኩባንያ አማካኝነት ለደንበኞቹ የሳተላይት የስልክ ቁሳቁሶችን ለመትከል ከሌላ ባልደርባ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ እንደነበር ተገልጿል።
ይሁንና ሁለቱ ኬንያውያን በጅጅጋ ከተማ በስራ ላይ እንዳሉ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ አገልግሎታቸውንም ግን ለማን ይሰጡ እንደነበር የታወቀ ነገር የለም።
በቃሊቲ እስር ቤት በእስር ላይ እንዳለ ህይወቱ ካለፈው ኬንያዊ በተጨማሪ ጀድሪክ ሙጎ የተባለ ሌላ የሃገሪቱ ዜጋ በእስር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም መገናኛ ብዙሃን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ በሁለቱ ኬንያውያን ከስልክ መሰረተ-ልማት ማጭበርበር ጋር በተገናኘ ክስ እንደተመሰረተባቸው ዘግበዋል።