ኬንያ በሰላም አስከባሪ ሃይል ስር በሶማሊያ ያሰማራችውን ጦሯን እንደምታስወጣ ገለጸች

ኢሳት (ኅዳር 12 ፥ 2009)

በሶማሊያ ተሰማርቶ በሚገኘው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል ውስጥ ወታደሮቿን አሰማርታ የምትገኘው ኬንያ ከሃገሪቱ ለቃ እንደምትወጣ ይፋ አደረገች።

ሃገሪቱ ሶማሊያ የሚገኘውን ጦሯን በማስወጣት ስትወስን ሶስተኛ ሃገር ስትሆን፣ ዩጋንዳና፣ ቡሩንዲ በቅርቡ ተመሳሳይ ውሳኔን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ፍራንሲስኮ ካታኖ፣ የኬንያ የሰላም አስከባሪ ሃይል ከአንድ አመት በኋላ ከሶማሊያ ለቆ መውጣት እንደሚጀምር ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ሃገሪቱ በሶማሊያ የሚገኙ ወታደሮቿን ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ ለማስወጣት ሁለት አመታትን ይፈጅባታል የተባለ ሲሆን፣ ወደ 20ሺ የሚጠጉ የሶማሊያ ወታደሮች ክፍተቱን እንዲሞሉ እንደሚደረግ ተወካዮች ገልጸዋል።

የኬንያ ተቃዋሚ ሃይሎች የሃገሪቱ መንግስት ወታደሮችን ከሶማሊያ እንዲያስወጣ ዘመቻን ሲያካሄዱ የቆዩ ሲሆን፣ መንግስት የወሰደው ውሳኔም ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ እንደሆነ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።

ኬንያ ከሶማሊያ ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ሲደርስበት የቆየን ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት በማድረግ ሰራዊቷን ወደ ኬንያ ማስገባቷ ይታወሳል።

ይሁንና የሃገሪቱ የተቃውሚ ፓርቲዎች መንግስት ሰራዊቱን ወደ ሶማሊያ ከማሰማራት ይልቅ ለሃገር ውስጥ ደህንነት ትኩረት መስጠት ይገባዋል ሲሉ ተቃውሞን ሲያቀርቡ እንደነበር ዘስታር የተሰኘ ጋዜጣ አመልክቷል።

ዩጋንዳና ቡሩንዲ በበኩላቸው ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የነበረ ሲሆን፣ ሁለቱ ሃገራት ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ወታደሮችን ማስወጣት እንደሚጀምሩ ይፋ አድርገዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ ሲሰጥ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ በ20 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉ ወታደሮቻቸውን በሶማሊያ ባሰማሩ ሃገራት ዘንድ ቅሬታ ማሳደሩም ይገልጻል።