ካናዳ በኢትዮጵያ ሁሉንም ያሳተፈ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲካሄድ ጠየቀች

ኅዳር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታዎች እያሳሰበው መምጣቱንና በሰላማዊ እና ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ የአገሪቱን ችግሮችን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ውይይቶች በማካሄድ ፖለቲካዊ ተሃድሶ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተነሱት ሕዝባዊ አመጾች ምክንያት ብዙ ዜጎች በመገደላቸው በአካባቢዎቹ አለመረጋጋቶች ተፈጥረዋል። ሁኔታዎቹ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው አስቀድሞ መፍትሔ እንዲበጅላቸው ሲሉ በካናዳ መንግስት የውጭ ጉዳይ  የንግድ እና እድገት ሚንስትሩ ስቴፋኒ ዲዮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት አሳስበዋል።  ካለፈ ዓመት ጀምሮ  በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሰላም ስጋቶች ተባብሰው መቀጠናቸውንም ሚንስትሩ አውስተው ፣ ይህም የካናዳ መንግስትን ስጋት ላይ እንደጣለው እና እያሳሰበው መምጣቱን ሚንስትሩ ገልጸዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚንስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ በዜጎች ላይ የሚደርሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይ እንዲሁም በአገሪቱ ትርጉም ያለው ሁሉንም የሚያሳትፍ አገር አቀፍ የሆነ የለውጥ ተሃድሶ እንዲደረግ አሳስበዋል።

በተለይም ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ እና ሁሉን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ የእድገትና የብልጽግና ስርዓት እንዲደረግ ሲሉ ሚንስትሩ በአጽኖት ጠይቀዋል። የሲቪክ ማኅበረሰቡ ለዴሞክራሲያዊ ለውጡ የሚያደርገውን አስተዋጾ አስመልክተው መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር እንዳለበት እንዲሁም ፖለቲካዊ ውይይቶችን በማድረግ የዴሞክራሲ ምኅርዳሩን ምቹ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰባቸውን አፍሪካ ኒውስ ግቧል።