ጥር 30 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ሂዩማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ብዙዎችን ለችግርና ለመከራ ህይወት ለዳረገውና ኢትዮጵያ እየፈፀመች ላለው የግዳጅ ሰፈራ የገንዘብ እርዳታ አድርጋለች ያላትን ካናዳን መውቀሱ ይታወሳል።
የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይፋ መሆን ፤ግብር ከፋዩን የካናዳ ህዝብ እያነጋገረ እንደሆነ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት፤ የአገሪቱ ታላቁ ራዲዮ የሆነው “ራዲዮ ካናዳ ኢንተርናሽናል” በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጡ ዘንድ፤ የድርጅቱን አንድ መርማሪ በመጋበዝ ፤እየሆነ ያለውን ነገር ካናዳውያን እንዲያውቁት አድርጓል።
ጋዜጠኛ ማርክ ሞንተጎመሪ ያነጋገራቸው የሂዩማን ራይትስ ዎች መርማሪ ፌሊክስ ሆርን፤ በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለው የግዳጅ ሰፈራ በስፋት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተስተዋሉበት እንደሆነ በማውሳት፤ ዜጎች ያለ ፍላጎታቸው ከቤታቸውና ከይዞታቸው ለተፈናቀሉበት የሰፈራ ፕሮግራም፤ የካናዳ መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መርዳቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
የካናዳ መንግስት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የሚሰጠውን እርዳታ በትክክል ሰብዓዊ መብቶችን ለማይጋፉ ነገሮች መዋላቸውን ጭምር ማረጋገጥ አለበት ያሉት ፌሊክስ ሆርን፤በካናዳ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ፤- “ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት” እየተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የሰፈራ ፕሮግራም ግን፤ የግብር ከፋይ ካናዳውያንን ገንዘብ- ኢ-ሰብዓዊ ለሆነ ተግባር ያዋለ ነው ብለዋል።
በተለይ በጋምቤላ ክልል ለህንድ፣ለሳኡዲ ዐረቢያ፣ ለቻይና እና በውጪ አገር ላሉ ኢትዮጵያውያን ሰፋፊ መሬቶችን ለመስጠት ተብሎ በተለያዩ አካባቢ የሚኖሩ እጅግ ብዙ ሰዎች ከቤታቸውና ከቀያቸው በግዳጅ መፈናቀላቸውን ያወሱት ተመራማሪው፤ የሰፈራ ፕሮግራሙን የተቃወሙትም – የተለያዬ በደሎች እየተፈጸሙባቸው በግዳጅ- ወዳልፈለጉትና ወደማያውቁት ቦታ መጋዛቸውን አመልክተዋል።
ፌሊክስ ሆርን አክለውም፦ካናዳ የሰብዓዊ መብቶችን ለገሰሰ ለዚህ ዓይነት አስገዳጅ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓ አግባብ እንዳልሆነ ፤እንዲሁም የሰጠችውን እርዳታ ኢትዮጵያ እንዴት እየተጠቀመችበት እንደሆነ ክትትል እንድታደርግ አሣስበዋል።