ካለ ምንም ፍርድ አንድ ዓመት ከአንድ ወር በእስራት የቆዩት አቶ ብስራት አቢ አሁንም አልተፈቱም
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 12 ቀን 2010 ዓ/ም) በሰማያዊ ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ብስራት አቢ ከአዲስ አበባ ለሥራ ጉዳይ ወደ ደሴ ከተማ በሄዱበት ታፍነው ከተወሰዱ አንድ ዓመት ከአንድ ወር ሞልቷቸዋል። እስካሁንም ምንም ዓይነት የፍርድ ብያኔ አላገኙም።
አቶ ብስራት ታፍነው ከተወሰዱ ከሁለት ወራት በኋላ ማእከላዊ እስር ቤት መኖራቸው ማወቃቸውን እንዲሁም ባለቤታቸውን አጠገባቸውን ተጠግተው የማናገር እድሉን መከልከላቸውን፣ አንዱ ልጃቸውም መታወቂያ የለህም ተብሎ አባቱን ለማየት መከልከሉን ባለቤታቸው ተናግረዋል።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ማርታ ባለቤታቸው ከታሰረበት እለት ጀምሮ ሶስት ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነቱ ጫና ለብቻቸው በመውደቁና ተእስር ቤት እየተመላለሱ ለመጠየቅ መቸገራቸውንም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ክስ ተከሰው አብረዋቸው የታሰሩት በነጻ ሲለቁ አለመለቀቃቸው እንዳሳዘናቸውና ባለቤታቸው ወንጀለኛ ባለመሆኑ ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች እንዲፈቱላቸው ሲሉ ወ/ሮ ማርታ ለሚመለከታቸው አካላት የተማጽኖ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አቶ ብስራት አቢ በእስር ቤት መርማሪዎች በማንነታቸው ላይ ያነጣጠሩ ስድቦችን ጨምሮ ኢሰብዓዊ ሰቆቃዎች እንደተፈጸመባቸውና የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል።
በሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማ የጥምቀት በዓልን በማክበር ላይ የነበሩ ሰላማዊ ምእመናንና የከተማ ነዋሪዎች በአጋዚና ወታደሮች የተፈጸመባቸውን የጅምላ ጭፍጨፋ የተቃወሙ በርካታ ሰዎች አሁንም ካለ ፍርድ በእስር ላይ ይገኛሉ። ከወልዲያ፣ መርሳ፣ ቆቦ፣ ሮቢትና አካባቢው ተይዘው ከታሰሩት እስረኞች መሃከል አንድ የስምንት ወር ነፍሰጡር መታሰሯም ታውቋል። እስረኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና ቢጠይቁም ሕጋዊ የዋስትና መብታቸውን ተነፍገው በእስር እንዲማቅቁ ተደርገዋል።
ከመርሳ ከተማ ተይዘው ከታሰሩ መሃከል ሰሜን ወሎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወልዲያ ምድብ ጅሎት ቀርበው ነበር። እስረኞቹ በሕዝባዊ ተቃውሞው ወቅት “ወያኔ ሌባ፣ በወያኔ አንገዛም!” የሚሉ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መፈክሮችን አሰምተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከመርሳ ከተማ ተይዘው በአንድ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 11 ተከሳሾች ውስጥአቶ ኃይሉ አስፋው፣ አቶ ጌታቸው ዓባይ፣ አቶ ደምሴ ክብረት፣ አቶ አያሌው ፀጋዬ፣ አቶ ሰማው መንገሻና እህታቸው ወርቅነሽ መንገሻ፣ አቶ ንጋቱ አየነው፣ አቶተስፋዬ ካሳዬ፣ አቶ ቢኒያም ዓለሙ፣ አቶ ሰይድ አያሌው እና አቶ ኤፍሬም እንደሚገኙበት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በፌስቡክ ገጹ ላይ ዘግቧል።