ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ የሚታየው ገንዘብ የማሸሽ እንቅስቃሴ ንግዱን እየጎዳ የኑሮውን ውድነትም እያባበሰው ነው ተባለ

ነሀሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአንድ የግል ባንክ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኛ ለኢሳት እንደገለጡት፣ የተለያዩ የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ባለፉት ሁለት ወራት ከዚህ በፊት ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ ገንዘባቸውን አሽሽተዋል። ይህንኑ ተከትሎም ንግድ ባንክ ለመድሀኒትና መሰረታዊ ለሚባሉት የፍጆታ እቃዎች መግዢያ ካልሆነ በስተቀር ፣ ማንኛውም ነጋዴ ሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዳይከፍት መመሪያ አስተላልፎአል። እገዳው በአገሪቱ የሚታየው የዶላር እጥረት እስከሚቀረፍ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚጸና ታውቋል።

ብሄራዊ ባንክም ሆነ ንግድ ባንክ እስካሁን ድረስ የሰጡት ይፋዊ የሆነ መግለጫ  ባይኖርም፣ የባንክ ሰራተኞች ግን ዶላር በገፍ ወደ ውጭ አገር እየተሸኘ መሆኑ ለችግሩ ዋነኛው መንስኤ ሆኗል ብለው እንደሚያምኑ የባንክ ሰራተኛው ገልጠዋል። የአቶ መለስ ዜናዊ የደህንነት ሁኔታ በውል አለመታወቅ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ለማሸሻቸው ዋነኛ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው ሰራተኛው ግምታቸውን ያሰፈሩት።

በግልጽ የሚታየው ነገር ይላሉ ሰራተኛው ” በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ዶላር ከአገር ጠፍቷል፤ ሁኔታውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሻሻል አይመስልም።”

መንግስት ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ ዶላር በጥቁር ገበያ ይሸጣሉ ብሎ የሚገምታቸውን ድርጅቶች ወደ ማሰስና እርማጃ ወደ መውሰድ ሊያመራ ይችላል በማለት አክለዋል።

የዶላር መጥፋት በእቃዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይ አድርጎታል።  መንግስት በአስቸኳይ የአቶ መለስን የጤና ሁኔታ ይፋ ማድረግ ካልቻለና የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማረጋጋት ካልቻለ አሁን የሚታየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል።

በሌላ ዜና ደግሞ በአማራ ክልል በርካታ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል

የኢሳት የአማራ ክልል ዘጋቢ እንዳለው በርካታ ነጋዴዎች ድርጅቶችን ለመዝጋት የተገደዱት ከግብር ጋር በተያያዘ ነው። በክልሉ የቁርጥ እና የአግልገሎት የሚባሉ ሁለት የግብር አከፋፈል መንገዶች ያሉ ሲሆን፣ መንገድ ላይ ፑል የሚጫውቱ ወታቶች ሳይቀር ፣ ግብር እንዲከፍሉ ተደርገዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የክልሉ የንግድ ቤቶች ታሽገው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል።

ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻው ከታሸጉባቸው በሁዋላ፣ መንገድ ላይ ያለስራ እንደሚያሳልፉ ታውቋል።

በዘፈቀደ እየተጣለ ያለው ግብር በክልሉ ከሚታየው ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ ህዝቡ በእጅጉ እንዲማረር አድርጎታል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide