(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 7/2010) በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ትጥቅ ለማስፈታት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ከ7 በላይ የመከላከያ ወታደሮች ተገደሉ።
በዞኑ አርማጭሆ ወረዳ ሮቢት ከተማ ትጥቅ ለማስፈታት የተንቀሳቀሱት የሕወሃት ወታደሮች ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር መጋጨታቸውም ታውቋል።
ሕዝቡ መሳሪያ ለማስፈታት በሕወሃት ታጣቂዎች ላይ በወሰደው ርምጃም ከ15 በላይ የአገዛዙ ወታደሮች ቆስለዋል።
በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የበርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ቤትን በሃይል ጥሶ በመግባት በሚደረገው የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ የሕወሃት ታጣቂዎች ከሕብረተሰቡ ጋር እየተጋጩ መሆናቸው ነው የተነገረው።
ትላንት መጋቢት 6/2010 በሰሜን ጎንደር ዞነ አርማጭሆ ወረዳ ሮቢት ከተማ ትጥቅ ለማስፈታት በተካሄደ ዘመቻ ታዲያ ከ7 በላይ የማዘዣ ጣቢያ/ኮማንድ ፖስት/ ወታደሮች በአካባቢው ሕብረተሰብ ተገድለዋል።
ይህም ጥቃት የደረሰው የአንድ አርሶ አደር ቤትን ሰብረው በመግባት ሕጋዊ ትጥቁን ለማስፈታት በተደረገ እንቅስቃሴ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወደ አርሶ አደሩ ቤት በምሽት የተንቀሳቀሱት የሕወሃት ወታደሮች በተከፈተባቸው የአጸፋ ጥቃት ከ7 በላይ ሲገደሉ ከ15 የሚበልጡ ደግሞ ቁስለኛ መሆናቸው ነው የተነገረው።
የተኩስ ልውውጡ እንደተሰማ በአካባቢው ሕብረተሰብ ድንገተኛ ጥቃት የደረሰባቸው ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ወታደሮቹ ድንገት ትጥቅ እንዲያስፈቱ በአገዛዙ ሲላኩ ያልገመቱት ጥቃት ስለደረሰባቸው ያልተጠና ተልዕኮ ተሰጥቶናል በሚልም በአዛዦቻቸው ላይ ተኩስ መክፈታቸውና እርስ በርስ መጋጨታቸውም ተነግሯል።
ጥቃቱን ያደረሱት የአካባቢው ነዋሪዎችም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ጫካ መግባታቸውን የኢሳት ምንጮች አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻው በአካባቢው ሕብረተሰብ ተጋድሎ እየተጨናገፈ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።