ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለሚደረግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ቢደረግም አልተሳካም። ፕሮጀክቱ በ2001 ዓም ተጀምሮ በ3 አመታት ውስጥ መጠናቀቅ ነበረበት።
ከብሮድካስት ባለስልጣን የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው ስራው ሊሳካ ያልቻለው በሙስናና በብልሹ አሰራር ምክንያት ነው። ሀገር አቀፍ የሬዲዮና የቴሌቭዥን የማስፋፊያ ማሻሻያ በ2001 ተጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመሳሪያ ግዥና የህንጸ ግንባታ ተጠናቆ የማሰራጫ መሳሪያዎቹን በመትከል ስርጭት ይጀምራል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ በሙስና ምክንያት የተገዡት መሳሪያዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆኑ ሥራው እስካሁን ሊሳካ አልቻለም፡፡
በዚህ የሙስና ቅሌት ውስጥ እጃቸው ያለበት ኃላፊዎች ተጠያቂ አልሆኑም። በኢትዮጵያ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ እንዲቋቋም ቀደም ሲል በ1991 ዓ.ም የወጣ አዋጅ በሁዋላም በ1999 ዓ.ም ተሻሽሎ በፓርላማው በወጣው አዋጅ ቁጥር 533/1999 ቢፈቅድም ከአናሎግ ወደዲጂታል የሚደረገው የቴክኖሎጂ ሽግግር መዘግየት ጋር በተያያዘ ለዓመታት ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
በሌላ ዜና ደግሞ የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ሃላፊ የሆኑት የህወሃቱ አቶ ዘርአይ አስጎደም በጋምቤላ ክልል በገነቡት ሆቴል ከህወሃት ደጋፊ ተቀናቃኞቻቸው ክስ እየቀረበባቸው ነው። ጸረ ሙስና በባለስልጣኑ ላይ የሚቀርበውን የሙስና ክስ ተንተርሶ ምርምራ ያድርግ አያድርግ የታወቀ ነገር የለም።
አቶ በረከት ስምኦን ስልጣናቸውን ከለቀቁ በሁዋላ የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤትን ሲመሩ የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን በቅርቡ በህወሃቱ አቶ ጌታቸው ረዳ ተቀይረዋል። የእርሳቸው ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማል በአዲሱ የሹመት አሰጣጥ በየትኛው የሃላፊነት ቦታ እንደተመደቡ አልታወቀም።