ግንቦት ፳፬ ( ሃያ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት ለቢቢሲ እንደገለጸው ከሆነ ሀምሳ የሚጠጉ ሰዎችን ይዞ በሳህራ በርሀ በመጓጓዝ ላይ የነበረ አንድ የጭነት ተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት በመሆኑ አርባ አራት ሰዎች በውሃ ጥም ህይወታቸው አልፏል።
የተረፉት ስድስት ሰዎች ረጅም የእግር መንገድ በመጓዝ በኒጀር ዲንኮ የቀይ መስቀሉ መስሪያ ቤት መድረሳቸውን የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ሲገልጹ የተረፉት ደግሞ ሁሉም ሴቶች ናቸው። ከሟቾቹም ውስጥ በርካታ ህጻናት እንደሚገኙበት ሲታወቅ ፣ጋናውያንና ናይጀሪያውያን እና በርካታ የአፍሪካ ቀንድ አገር ዜጎች ወደ አውሮፓ ለመውጣት ይህንን መንገድ ይጠቀሙበታል።
የኒጀር ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንደገለጹት ባለፈው ሰኔ ወር የሰላሳ አራት ስደተኞች አስከሬን በኒጀርና አልጀሪያ ድንበር የተገኘ ሲሆን፣ ሀያ ያህሉ ህጻናት ነበሩ። ይህንኑ መንገድ ሲጠቀሙ የሞቱትን ሲደተኞችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ አዳጋች መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።