ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የማበረታቻ መድሃኒት ምርመራ ሊያካሄድባቸው መሆኑ ተነገረ

ኢሳት ( መጋቢት 29 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ አትሌቶች በውድድር ወቅት የተከለከሉ ማበረታቻ መድሃኒቶች ተጠቅመዋል የሚለው መረጃ ይፋ መደረግን ተከትሎ ከ300 በላይ አትሌቶችን ምርመራ ሊያካሄድባቸው መሆኑ ተገለጠ።

የአለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ሃገሪቱ መጠነ ሰፊ የምርመራ ዘመቻን ካላካሄደች ከአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ስትታገድ እንደምትችል ሃሙስ ማሳሰቡን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙህን ዘግበዋል።

የአለም አቀፉ የጸረ-ማበረታቻ ኤጄንሲ በአሁኑ ወቅት በስድስት የኢትዮጵያ አትሌቶች ላይ ምርመራ እያካሄዱ ሲሆን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር በበኩሉ ከ350 የሚበልጡ አትሌቶች ላይ ተመሳሳይ ምርመራ እንደሚያካሄድ ይፋ አድርጓል።

በጉዳዩ ዙሪያ መግልጫን የሰጡት የማህበሩ ሃላፊዎች የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበርና የአለም አቀፍ የጸረ-ማበረታቻ ኤጄንሲ ለኢትዮጵያ ጠንካራ ማሳሰቢያ መስጠቱን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

የማህበሩ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ስለሺ ብስራት የተከለከሉ ማበረታቻ መድሃኒቶችን የተጠቀሙ አትሌቶች በመገኘታቸው ምክንያት ሃገሪቱ ልዩ ክልትትል ውስጥ መውደቋን አስታውቀዋል።

ምርመራ የሚካሄድባቸው ከ350 በላይ አትሌቶችም በቀጣዮቹ ሰባት ወራት ውስጥ ውጤታቸው የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ውጤቱም ለአለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የጸረ-ማበረታቻ ኤጄንሲ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የሁለቱ አለም አቀፍ ተቋማትም በሰኔ ወር በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማካሄድ 300ሺ ዶላር (ስድስት ሚልዮን ብር በላይ) እንደሚያስፈልግም አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የተከለከሉ ማበረታቻ መድሃኒቶችን በውድድር ወቅት ተጠቅመዋል የተባሉ በርካታ የሩሲያና የኬንያ አትሌቶች ከአለም አቀፍ መድረክ መታገዳቸው ይታወሳል።

ባለፈው ወር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተጠረጠሩ ሶስት አትሌቶችን ያገደ ሲሆን፣ ዘጠኝ የሚሆኑ ተጨማሪ አትሌቶችም በአለም አቀፍ አካላት ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ አለም አቀፍ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ኢትዮጵያ በተስጣት ጊዜ ምርመራን አጠናቃ የማትጨርስ ከሆነም የሩሲያና የኬንያ እድል ይገጥማታል ተብሎ ተሰግቷል።